ያለፈቃድ መንገድ ያጸዳው ናይጄሪያዊ ስደተኛ ቅጣቱ ተነሳለት

በሰሜናዊ ጣልያን በምትገኝ ከተማ ፈቃድ ሳያገኝ መንገድ አጽድቷል በሚል ቅጣት ተጥሎበት የነበረው ናይጄሪያያዊ ስደተኛ በነዋሪዎች ጥያቄ ቅጣቱ እንዲነሳለት ተደረገ።

የ29 ዓመቱ ስደተኛ ስራ አጥ ሲሆን፣ አላፊ አግዳሚውን ቁጭ ብሎ ገንዘብ ከመጠየቅ ሌላው ቢቀር መንገዱን አጽድቼላቸው ገንዘብ ቢሰጡኝ ብዬ ነው ተግባሩን የፈጸምኩት ብሏል።

ያለፈቃድ መንገዱን በማጽዳቱም 383 ዶላር (11ሺ ብር አካባቢ) እንዲቀጣ ተወስኖበት ነበር። ነገር ግን የከተማዋ ነዋሪዎች ውሳኔውን በመቃወማቸው የከተማዋ ምክር ቤት ቅጣቱን አንስቻለሁ ብሏል።

ጉዳዩን የሰሙ ጣልያናውያንም በማህበራዊ ሚዲያ ሰዎችን በማስተባበር የቅጣቱን ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረት አድርገዋል።

ናይጄሪያዊው መንገድ ሲያጸዳ የነበረው '' ምንም አይነት ልመና ውስጥ ሳልገባ በታማኝነት ከማህበረሰባችሁ ጋር መቀላቀል እፈልጋለሁ፤ መንገዶቻችሁን ንጹህና ማራኪ አደርግላችኋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ለስራዬ ትንሽ ትከፍሉኛላችሁ'' የሚል መልእክት በወረቀት ላይ ጽፎ ነበር።

መጀመሪያ ላይ ጉዳዩን በማህበራዊ ሚዲያ ይዞት የወጣው ማቴዎ ዲ አንጀሎ የተባለ ጣልያናዊ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልእክት '' ቅጠሎች፣ የሲጋራ ቁራጭ እና ሌሎች የምንጥላቸው ቆሻሻዎች የውሃ መፍሰሻውን እየደፈኑት ነበር፤ ይህ ግለሰብ ይህንን ችግር ነው ያቃለለልን'' ብሏል።

ናይጄሪያዊው ግለሰብ የፖሊስ አይን ውስጥ የገባው በአካባቢው የነበሩ አንዳንድ ነዋሪዎች ቅሬታ በማሰማታቸው ነበር።

ነገር ግን ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ ምክር ቤት ስልክ በመደወል ግለሰቡ ምንም ያጠፋው ነገር እንደሌለ በመግለጻቸው ምክንያት ቅጣቱ እንዲነሳ መደረጉ ታውቋል።

ምክር ቤቱም ቅጣቱን ያስተላለፉት ለስራው አዲስና ልምድ የሌላቸው የፖሊስ አባላት መሆናቸውን አስታውቋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)