በኮንጎ የ’ሕገወጥ’ የማዕድን ፈላጊዎች ላይ ጉድጓድ ተደርምሶ በርካቶች ሞቱ

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ወርቅ በሕገወጥ መንገድ ሲያወጡ የነበሩ ሰዎች ላይ ጉድጓድ ተደርምሶ ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

የመንግሥት አስተዳደር ሚኒስትር የሆኑት ስቲቭ ምቢካዪ እንዳሉት፤ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ጉድጓዱ ውስጥ አፈር ተደርምሶባቸው የቀሩ ካሉ በሚል ፍለጋው እንደቀጠለ ነው።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሕገ ወጥ ማዕድን ፈላጊዎች ላይ እንዲህ አይነት አደጋ የተለመደ ሲሆን፣ የደህንነት መጠበቂያዎችም እጅጉን ኋላ ቀር ናቸው ተብሏል።

ምቢካዪ በትዊተራቸው ላይ እንዳሉት ከሆነ የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም ሊጨምር ይችላል።

የዜጎች መብት ተሟጋች የሆነው ጀስቲን ኪያንጋ አሱማኒ፣ አደጋው ረቡዕ ረፋዱ ላይ መድረሱን ገልጾ፣ ማዕድን አውጪዎቹ እየቆፈሩ የነበረው ማኔይማ በተሰኘቸው ግዛት እንደነበር ተናግሯል።

አደጋው በደረሰበት ወቅት "እድሜያቸው 18 ያልሞላ ታዳጊዎችና ነፍሰጡር ሴቶች በስፍራው ማዕድን ፍለጋ ላይ ተሰማርተው ነበር" ሲል አክሏል።

በሰኔ ወር ላይ በኮንጎዋ ሉአላባ ግዛት፣ ኮፐርና ኮባልት ማዕድን እየፈለጉ የነበሩ በርካቶች ጉድጓድ ተደርምሶባቸው መሞታቸው ይታወሳል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ የመዳብ፣ ኮባልት፣ ዳይመንድ፣ እና ወርቅ ክምችት ያላት ብትሆንም ሕዝቦቿ ግን ዛሬም በከፋ ድህነት ስር ይኖራሉ።

በማዕድን በበለፀጉ አካባቢዎች በሕገወጥ መልኩ የሚደረጉ የማዕድን ፍለጋዎች የተስፋፉ ሲሆን፣ ይህንን ለማስቆም በፀጥታ ኃይሉ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ ፍሬ አልባ ሆነው ቀርተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።