አሜሪካ በኢራን ላይ ያስተላለፈችውን ማዕቀብ አገራቸዉ እንደማትቀበል የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታወቁ

የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይደር አል-አባዲ አሜሪካ በኢራን ላይ ያስተላለፈችውን ማዕቀብ ባግዳድ ሙሉ ለሙሉ እንደማትቀበል አስታወቁ፡፡

ሀገሪቱ በኢራን ላይ ከጣለቸው ማዕቀብ መካከል ከቴህራን ጋር ለሚኖራት የንግድ ልውውጥ ዶላርን አንደማትጠቀም አስታዉቃለች፡፡

አሜሪካ ሀያላን ሀገራት በፈረንጆቹ 2015 ከአራን ጋር በኒዩክለር መርሐ ግብር የገቡትን ውል ማቋረጧን ተከትሎ በቴህራን ላይ ዳግመኛ እቀባ አስተላለፋለች፡፡

በመሆኑም ኢራን የነዳጅ ሀብቷን ለሌሎች ሀገራት እንዳትሸጥና አጎራባች ሀገራትም የንግድ ልውውጥ እንዳያደርጉ አሜሪካ ገደብ ብታደርግም ኢራቅ አሁን ላይ ከቴህራን ለሚኖራት ግብይት ዶላርን ብቻ ለግብይት አንደማታውል አል-አባዲ አሰታውቀዋል፡፡

አል-አባዲ በባግዳድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ውሳኔውን ያስተላለፉት በቴህራን የሚኖራቸው ይፋዊ ጉብኝት በኢራን በኩል መሰረዙን አስመልክቶ የተሰማውን ዜና ተከትሎ አንደሆነ ታውቋል፡፡

አስቀድሞም ከሳምንት በፊት የአሜሪካን እቀባ እንቀበላለን ሳይሆን ባግዳድ ከቴህራን ለሚኖራት ግብይት ዶላር ጥቅም ላይ አይውልም ማለታቸውን በመግለጫው አስታውሰዋል፡፡

ኢራቅ ከኢራን የተለያዩ ምርቶችን ማስገባቷን ታቆማለች ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄም መንግስታቸው ጉዳዩን እያጤነው መሆኑን አሰረድተው፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታም የተሰጠበት ውሳኔ አለመኖሩን ፍንጭ ሰተዋል፡፡

አል-አባዲ አክለውም አሜሪካ በኢራን ላይ ባስተላለፈችው ማዕቀብ ተቀባይነት እንደሌለው ባሳለፍነው ሳምንት መግለፃቸውን ያስታወሱ ሲሆን አቋማቸውም የባግዳድን ፍላጎት ማስጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋሺንግተን ቴህራን የኒዩክለር መርሀ ግብሯን እንድታቋርጥና ለሽብርተኛ ቡድኖች የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንድታቆም ብሎም የባላስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራሟን እንድትዘጋ በሚል በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኩል ማዕቀብ አስተላልፋለች፡፡

አሜሪካና ኢራን የኢራቅ ሁነኛ ወዳጅ መሆናቸው የሚነገር ሲሆን ባሁኑ የአል-አባዲ ውሳኔ ማንገራገር ተከትሎ የባግዳድ አስተዳደር አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል በመዘገብ ላይ ነው፡፡ (ምንጭ፤ አልጀዚራ)