ቻይናና አውሮፓ ህብረት በሲቪል አቪየሽን ደህንነትና በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ቻይናና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በሲቪል አቪየሽን ደህንነትና በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ባሳለፍነው ወር በቻይና አውሮፓ የሁለትዮሽ መድረክ ላይ በመሪዎች ደረጃ የተደረሰው ስምምነት ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ አንደሚችል ዘገባው አመላክቷል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ወገኖች የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የጠቀሱት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ጄን ክላውድ ጀንከር በዚህ ባልተረጋጋ አለም የአውሮፓና የቻይና የሁለትዮሽ ትብብር መጠናከር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም የአውሮፓ ህብረት የአለም ሀገራት ተባብረው ከሰሩ አለምን ጠንካራ፣ ምቹ፣ ከደህንነት ስጋት የጸዳችና የበለጸገች ለማድረግ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በጽኑ ያምናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቶቹ የስራ እድል ከመፍጠርና እድገትን ከማፋጠን ባሻገር ሁለቱን አህጉሮችና ህዝቦች ይበልጥ ለማቀራረብ ያግዛሉ ያሉት ጄን ክላውድ ጀንከር የተጀመረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የቻይና ሲቪል አቪየሽን አስተዳደር ኃላፊ ፌንግ ዜንግሊን በበኩላቸው የተፈረሙት ስምምነቶች የቻይናና የአውሮፓን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቶች ሁለቱ ወገኖች በአቪየሽን መስክ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለመለዋወጥና ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ያግዛሉ ያሉት ኃላፊው የሁለቱን ወገኖች የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ቻይናና የአውሮፓ ህብረት ለዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችና ግልጽ የሆነች አለምን ከመፍጠር አኳያ የማይቀየር አቋም እንዳላቸውናት በአቪየሽኑ መስክ በትብብር ለመስራ የደረሱት ስምምነት የዚህ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡ (ምንጭ፡-ሲጂቲኤን)