የቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ዳግም ወደ በረራ ይመለሳሉ ከተባለው ጊዜ ሊዘገዩ እንደሚችሉ ተገለጸ

የቦይንግ 737 አዉሮፕላኖች በአሜሪካ ሰማይ ዳግም ወደ በረራ ይመለሳሉ ከተባለዉ ጊዜ ሊዘገዩ እንደሚችሉ የአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር አስታወቀ።

ምንም እንኳን አዉሮፕላኖቹ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ሰኔ ወር ማገባደጃ ላይ አልያም በሀምሌ ወር መጀመሪያ አከባቢ ዳግም ወደ በረራ ይመለሳሉ ተብሎ የተገመተ ቢሆንም ከበበረራ እገዳ ጋር ተያይዞ ሊዘገይ አንደሚችል ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጀነራል ዳን ኤልዌል አዉሮፕላኖቹ ላይ የተጣለዉን የበረራ እገዳ ለማንሳት አንድ አመት ቢያስፈልግ እንኳን ጊዜዉን መጠበቅ ግዴታ በመሆኑ በረራው ሊዘገይ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

እንግሊዝና ቻይናን ጨምሮ ከ33 የአለም ሀገራት የተዉጣጡ አለም አቀፍ የአቪየሽን ተቆጣጣሪዎችም አዉሮፕላኑ ዳግም ወደ ስራ በሚመለስበት ሁኔታ ላይ በአሜሪካ ምክክር እያደረጉ ናቸዉ ተብሏል።

አዉሮፕላኖቹ ዳግም ወደ ስራ ከመመለሳቸዉ አስቀድሞ በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት ዉስጥ የሙከራ በረራ እንደሚካሄድ የአሜሪካ የአቪየሽን አስተዳደር ያስታወቀ ሲሆን፣ ሌሎች በአዉሮፕላኑ ላይ እገዳ የጣሉ ሀገራት ግን አዉሮፕላኑን መች ወደ ስራ እንደሚመልሱት የታወቀ ነገር የለም።

ቦይንግ 737 አዉሮፕላን በአምስት ወራት ጊዜ ዉስጥ በኢንዶኔዢያና በኢትዮጵያ ባጋጠሙት ሁለት አደጋዎች ከ346 ሰዎች በላይ መሞታቸዉን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ የአለም ሀገራት አዉሮፕላኑን ከበረራ ማገዳቸዉ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም አምራቹ ኩባንያ በአዉሮፕላኖቹ ላይ የሶፍትዌር ማሻሻያ ማድረጉ የሚታወስ ነዉ ሲል የዘገበዉ ቢቢሲ ነዉ።