ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን እክል እንዳጋጠመውና የሙከራ በረራ ማድረግ እንዳማይችል ተገለጸ

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳዳሪ [ኤፍኤኤ] ቦይንግ 737 ማክስ የተሰኘው አውሮፕላን እክል እንዳጋጠመውና የሙከራ በረራ ማድረግ እንዳማይችል አስታውቋል።

በቦይንግ አውሮፕላን ማምረቻ ታሪክ ከፍተኛ ሽያጭ አስገኝቶ የነበረው ማክስ 737 ሞዴል አውሮፕላን በተከታታይ ከደረሰበት አደጋ በኋላ ሽያጩ ቀንሷል።

አውሮፕላኑን የገዙ አየር መንገዶች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ በኋላ 737 ማክስ አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርገዋል።

ከኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች አደጋ በኋላ ቦይንግ ማክስ 737 ተብሎ የሚጠራውን ሥሪት 'ሶፍትዌር' (ውስጣዊ አሠራር) ለማደስ ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል።

እድሳቱ ተጠናቆ የመኩራ በረራ ያደርጋል ተብሎ የተጠበቀው ቦይንግ 737 ግን አሁንም ችግር እንዳልተለየው ነው የተሰማው።

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳዳሪ ችግሩ ምን እንደሆነ በውል ባያስቀምጥም '737 ማክስ መብረር አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ቦይንግ አሁንም ችግሩን ቢያጤነው' ሲል ተደምጧል።

ባለፈው ወር ተቆጣጣሪው አካል (ኤፍኤኤ) ቦይንግ እድሳቱን ካጠናቀቀ ወርሃ ሐምሌ ላይ የሙከራ በረራ ማድረግ ይችላል ብሎ ነበር።

የአውሮፕላኑ ዋነኛ ችግር አፍንጫውን ወደፊት አድርጎ ወደታች እንዳይምዘገዘግ የሚያደርገው ሶፍትዌር እንደሆነ የሚናገሩት ባሉሙያዎች ቦይንግ ይህንን ችግር ሊቀርፍ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ።

ከባለሙያዎች የተለያዩ መላምቶች እየተሰነዘሩ ቢሆንም ቅሉ አሁን ማክስ 737 የገጠመው ችግር በውል የሚታወቅ አይደለም።

ኤፍኤኤ የተሰኘው ተቆጣጣሪ አካል እድሳቱ በቂ አይደለም ብሎ ካሰበ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ሰማይ ላይ የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደምሆንም ተገምቷል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ)