የአሜሪካና ቻይና የንግድ ግንኙነት በተሻለ መንገድ ለመጀመር አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ገለጹ

የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት መርገቡንና የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት በተሻለ መንገድ ለመጀመር አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ፡፡
አሜሪካና ቻይና በተለያዩ የንግድ ጉዳዮች በርከት ላለ ጊዜ አብረው ሲሰሩ የቆዩ ሀገራት ቢሆኑም የሁለቱ ሀገራት የንግድ ፍጥጫ ከጀመረ ግን ሰነባብቷል፡፡
በተለይ ፕሬዚዳት ዶናልድ ትራም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የነዚህ ሀገራት የንግድ ጦርነት የዓለምን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡  ሁኔታው የዓለም ሀገራትን ትኩረት የሳበው የዓለም ምጣኔ ሀብት ችግር ውስጥ ይከታል ተብሎ በመታመኑ ነው፡፡ 
ሀገራቱ የተፈጠረው ችግር እንዲቀረፍ በሚል በተለያዩ ጊዚያት የተለያዩ ውይይቶችን ቢያደርጉም ከመፍትሄ መድረስ ግን አልቻሉም፡፡
ከዚህ ቀደም አሜሪካ ከቻይና በምታስገባቸው 50 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። ሌሎች 200 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ላይ ደግሞ 10 በመቶ ታሪፍ መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡ 
ቻይና በበኩሏ ከአሜሪካ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ 50 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ አጸፋ ታሪፍ ጥላለች። ሌሎች 60 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦችም በተመሳሳይ 10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ ተጭኖባቸዋል።
ሰሞኑን በጃፓኟ ኦሳካ ከተማ በተካሄደው የቡድን ሃያ ሀገራት ስብሳባ ለይ የተገናኙት የአሜሪካ እና የቻይና መሪዎች የሁለቱን ሀገራት የንግድ ፍጥጫ ማርገብ የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል፡፡ ውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ፍጥጫ ላይ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናድ ትራምፕ ገልፀዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከሀገራቱ የንግድ ውዝግብ ባሻገር የሁለቱ ሀገራት የንግድ ጦርነት በዓለም ዓቀፉ ኢኮኖሚ ዙሪያ ያሳረፈው ተጽዕኖ ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል፡፡
ይህንን ችግርም ለመፍታት በቀጣይም መሰል ውይይቶች እንደሚኖሩ የተገለፀ ሲሆን፣ በተለይም ቀረጥን በተመለከተ በአሜሪካ በኩል አዲስ የሚሻሻሉ ነጥቦች አንደሚኖሩም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልፀዋል፡፡ (ምንጭ፡-ሲ ኤን ኤን)