ቦይንግ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች መቆም ያጋጠመው ኪሳራ 5 ቢሊየን ዶላርን ተሻግሯል

ቦይንግ በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች ንብረት በሆኑ ሁለት 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ባጋጠመ አደጋና ያንን ተከትሎ አውሮፕላኑ ላይ በተገኘ ችግር ምክንያት በርካታ አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደዋል፤ በዚህም ከፍተኛ ኪሳራ ገጥሞታል፡፡

ቀደም ሲል ቦይንግ በቴክኒክ ስጋት እንዲቆሙ ባደረጋቸው አውሮፕላኖቹ የገጠመውን ኪሳራ ለማወራረድ የመደበው በጀት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነበር፡፡

ይሁንና በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ተፈትቶ አውሮፕላኖቹ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ባለመሳካቱ ለበለጠ ኪሳራ መዳረጉ ተሰምቷል፡፡ በዚህም ቦይንግ በታሪኩ የከፋ ለተባለ ኪሳራ መጋለጡን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች አደጋ ዙሪያ ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶች እንዲሻሻሉና ሶፍትዌሮች እንዲሻሻሉ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

የበረራ ፈቃድ አለማግኘቱን ተከትሎ ቦይግ ወርሃዊ የአውሮፕላን ምርቱን በ10 አውሮፕላኖች ቀንሷል፡፡ በዚህም አውሮፕላን ላዘዙና ርክክብ ለዘገየባቸው ሀገራት ሳይቀር ካሳ ለመክፈል ተገድዷል፡፡

ቦይንግ ከበረራ ባለስልጣናት ጋር እየተወያዬ መሆኑን ገልጾ፤ እስከ 2019 (እ.አ.አ) የመጨረሻ ሩብ ዓመት ወደ በረራ ለመመለስ እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ሆኖም አሁን ከገጠመው ኪሳራ አንፃር ኩባንያው ወደ በረራ የመመለሻ ጊዜው ከዚህ የበለጠ ሊዘገይ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡