ኢራን በባህረ ሰላጤ ‘ህገወጥ’ የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከብ መያዟ ተገለፀ

ኢራን በባህረ ሰላጤ ህገወጥ ነው ያለችውን የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከብ መያዟን የሀገሪቱ ሚዲያ አስታውቋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ኮማንደር በባህረሰላጤው በኩል ለአረብ ሀገራት በህገወጥ መንገድ ነዳጅ ዘይት ሊያስገባ ሲል መያዛቸውን መግለፃቸው ነው የተዘገበው፡፡
መርከቧ ከ700 ሺ በላይ ሊትር ነዳጅ ዘይት ስትንቀሳቀስ እንደነበርና ሰባት የመርከቧ ሰራተኞች አብረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
ኢራን በህገወጥ መንገድ የነዳጅ ዘይት ይዣለሁ ስትል ይህ ሁለተኛው ነው፤ ከሳምንታት በፊትም የኢራን የባህር ጠረፍ ጠባቂ የፓናማ ሰንደቅ አላማ የነበራትን መርከብ አግተው ነበር።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ በድረገፁ እንዳሳወቀው፣ በወቅቱ መርከቧ የተያዘችው የባህር ኃይሉ የተደራጀ ህገወጥ የነዳጅ ዘይት ዝውውርን ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት ነው።
ባለፈው ወርም የእንግሊዝ ባንዲራን ታውለበልብ የነበረች ነዳጅ ጫኝ መርከብ በሃርሙዝ ስርጥ የውሃ ክልል ላይ እንደታገተች ነው።
አሜሪካ እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2015 በሁለቱ ሀገራት የተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት ራሷን ካገለለች በኋላ በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሏን ተከትሎ በባህረ ሰላጤው አካባቢ ውጥረት መንገሱ ተገልጿል።
በኦማን ባህረ ሰላጤ ለተፈፀሙ ሁለት የተለያዩ የነዳጅ መርከብ ጥቃቶች አሜሪካ ኢራንን መወንጀሏ የሚታወስ ነው።
በሃርሙዝ የቀጠና የበረራ ቅኝት ላይ የነበረ ሰው አልባ የአሜሪካ አውሮፕላን መትታ የጣለችው ኢራን በበኩሏ ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።
እስካሁን ድረስ ነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቧ ባለቤትነት ያልታወቀ ሲሆን፣ የፋርስ ዜና ወኪል እንደዘገበው መርከቧን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ የተከናወነው ባለፈው ረቡዕ እለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የመርከቧ ሰራተኞች ዜግነታቸው ግልፅ አልተደረገም።
ነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቧ ቡሸህር የሚባል ቦታ የተወሰደች ሲሆን፣ ነዳጁም ለባለስልጣናቱ እንደተላለፈም ዘገባው ጨምሮ አስነብቧል።
ከየትኛውም ሀገርም መርከቤ ጠፍቶብኛል ወይም ታግቶብኛል የሚል መግለጫም እንዳልወጣም ተገልጿል።
የቢቢሲ አረብኛው ኤዲተር ሰባስቲያን የነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከቧ ምንም እንኳን ትልቅ ባትሆንም በቀጠናው ያለውን ውጥረት ሊያባብሰው እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)