የዝሆን ግልገሎች ለዓለም አቀፍ ንግድ እንዳይቀርቡ እገዳ ተጣለ

የዝሆን ግልገሎች ለዓለም አቀፍ ንግድ እንዳይቀርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መታገዳቸው ተገለጸ፡፡

በስዊዘርላንድ ጀኔቫ በተካሄደው ጉባዔ ከአፍሪካ የዝሆን ግልገሎችን በመያዝ ለእንስሳት ማቆያ እንዳይሸጡ የሚከለክለው ሕግ ፀድቋል።

አደጋ ላይ በሚገኙ የእንስሳት ዝርያዎች ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የሚያተኩረው ጉባዔ ተሳታፊዎች በጉዳዩ ላይ ለቀናት ከተከራከሩበት በኋላ ሕጉን ለማጥበቅ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።

እግዱ በ87 አብላጫ ድምፅ ድጋፍ እና በ29 ተቃውሞ ካገኘ በኋላ እግዱ እንዲፀድቅ ተወስኗል። ይሁን እንጂ ዝሆኖችን ወደ ውጭ በመላክ የምትታወቀው አፍሪካዊት ሃገር ዚምባብዌ ልክ እንደ አሜሪካ ሁሉ እግዱን ተቃውማለች።

ዚምባብዌ እንቅስቃሴውን አጥበቃ በዘመቻ ስትቃወም የነበረ ሲሆን፣ የአውሮፓ ሕብረትም በዓለም ላይ ያለውን የእንስሳት ዝርያ ስብጥር እንዳይኖረው ያደርጋል ሲሉ መጀመሪያ አካባቢ ተቃውመውት ነበር።

ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዝሆን በብዛት የሚገኝባቸው ዚምባብዌና ቦትስዋና 'ተቀባይነት ላላቸውና ትክክለኛ ለሆኑ' ተቀባይ ሃገራት ዝሆኖችን ወደ ውጭ ለመላክ ይፈቅዱ ነበር።

በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ዝሆኖች የሚገኙባት ቦትስዋና በዚህ በያዝነው ዓመት ዝሆኖችን ማደን የሚከለክለው ሕግ፣ ገበሬዎችንና ከዚህ በፊት በማደን ገቢ ያገኙ የነበሩ ግለሰቦችን እየጎዳ ነው በሚል መፍቀዷ ይታወሳል።

እነዚህ ሃገራት ከጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2012 ጀምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ የዝሆን ግልገሎችን በመያዝ ለቻይና የእንስሳት ማቆያ መላካቸውን ሁዩማን ሶሳይቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።

በመሆኑም ትናንት የተላለፈው ውሳኔ የዝሆን ንግድን ቁጥጥር እንዲጠብቅ ያደርጋል ተብሏል።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ዝሆኖች ከዱር ተይዘው በእንክብካቤ በሚቆዩበት በየትኛውም የዓለማችን አካባቢ መቆየት የሚችሉ ሲሆን ይህ ግን የሚቻለው በከተማዋ የኮሚቴ አባላት ሲፀድቅ ይሆናል።

ይሁን እንጅ የአውሮፓ ህብረት በልዩ ሁኔታ መላክ እንደሚቻልና በእንስሳት ማቆያ ያሉ ዝሆኖችን ማዛወር እንደሚቻል ሕጉ የተወሰነ መሻሻል ከተደረገበት በኋላ ሃሳቡን ቀይሯል።

"ይህ ማለት አንድም ዝሆን ከዱር ተይዞ በውጭ አገር ለእንስሳት ምቹ በሆኑ ማቆያዎች አይገቡም ማለት አይደለም" ሲሉ የቦርን ፍሪ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ዊል ትሬቨርስ ተናግረዋል።

አክለውም እግዱ በተለይ በወደ ሩቅ ምስራቅ በጅምላ ያለ አግባብ የሚላኩ ዝሆኖችን ለመቆጣጠር ሕጉን ማጥበቅ አስፈላጊ እንደሆነም ገልፀዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)