አርጀንቲና ከምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ለማገገም የገንዘብ ቁጥጥር ህግ አወጣች

አርጀንቲና ከገጠማት የምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ለማገገም እና ገበያውን ለማረጋጋት ያስችላል ያለችውን አስገዳጅ የገንዝብ ዝውውር መቆጣጠሪያ ህግ ማውጣቷ ተገለጸ፡፡

መንግስት በቀጣይ የውጪ ገንዘቦችን ልውውጥ መጠንም ይገድባል የተባለ ሲሆን፣ ሀገሪቷ የገጠማትን የምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ለመቋቋም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ጋር እዳውን በምታስተላልፍበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ፍላጎት እንዳላት ተጠቁሟል፡፡

መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ ‹‹የምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴውን የተረጋጋ ለማድረግ፣ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ፣ ለሽማቾች ጥበቃ እና ቀጣይነት ያለው የግብይት ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊ የምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡

የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክም ‹‹የውጪ ምንዛሬውን የተረጋጋ›› ለማድረግ ርምጃው አስፈላጊ እንደሆነና ዜጎች በወር ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ለመግዛት ከፈለጉ ፈቃድ ማግኘት ግድ እንደሚላቸው ገልጿል፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሪሺዮ ማክሪ በአውሮፓዊያኑ 2015 በምርጫ ወደ መሪነት ሲመጡ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ በነፃ ገበያ መርህ እንደሚቀይሩ ቃል መግባታቸው ይታወቃል፤ ነገር ግን በተለይም በ2019 አጋማሽ ላይ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከ 22 በመቶ በላይ ማሻቀቡን ተከትሎ የገቡትን ቃል አጥፈው አስፈላጊ ነው ያሉትን ምጣኔ ሀብታዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገድደዋል ነው የተባለው፡፡ (ምንጭ፡- ቢቢሲ)