በሳዑዲ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ በየዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ።

ቅዳሜ ዕለት በሁለት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ቦታዎች ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ለዓለም የሚቀርበው የነዳጅ መጠን አምስት በመቶ ቀንሷል።

በዚህም ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከ15 እስከ 19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በድሮን ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው የሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ወደ ቀደመ ስራቸው ለመመለስ ሳምንታት ያስፈልጋል ተብሏል።

ቅዳሜ ዕለት ጥቃት የተሰነዘረባቸው የሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት በዓለማችን እጅግ ዘመናዊ እና ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው የነዳጅ ማቀነባበሪያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የድሮን ጥቃቱን የፈጸምነው እኛ ነን ቢሉም አሜሪካ ግን ሳዑዲ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርጋለች።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ቅዳሜ ዕለት የሳዑዲ ነዳጅ ማውጫ ተቋማት ላይ ለተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከምዕራባውያን መንግሥታት ድጋፍ የሚያገኘው ሳዑዲ መራሹ ኃይል በየመን እየተደረገ ባለው ጦርነት ለየመን መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ኢራን ደግሞ ለሁቲ አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ማይክ ፖምፔዮ ''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢኔርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው'' ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ለጥፋቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ስለምናውቅ "አቀባብለን" የሳዑዲ መንግሥት ምክረ ሃሰብ ምን እንደሆነ እየጠበቅን ነው ብለዋል።

የሳዑዲ ባለስልጣናት ጥቃቱ በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም በማለት የድሮን ጥቃቱ ስላደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል። የተሰነዘረው ጥቃት የሳዑዲ አረቢያን የድፍድፍ ነዳጅ የማምረት አቅም በግማሽ መቀነሱ ግን ተረጋግጧል።

ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች ስትሆን፣ በየቀኑ ወደ 7 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጪ ሃገራት ትልካለች። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)