የሳዑዲው ልዑል ኢራን ለዓለም ነዳጅ ምርት ስጋት ናት አሉ

የሳዑዲ አረቢያው ልዑል መሃመድ ቢን ሳልማን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢራን ከድርጊቷ እንድትታቀብ ማድረግ ካልቻለ የነዳጅ ዋጋ በማይታመን ሁኔታ ይጨምራል ሲሉ አስጠነቀቁ።

በሳዑዲ አረቢያና በኢራን መካከል የሚደረግ ጦርነት ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ ሥርዓትን ሊያቃውስ ይችላል ብለዋል።

ለዚህም መነሻ የሆናቸው ከሁለት ሳምንት በፊት በሳዑዲ ሁለት የነዳጅ ማምረቻ ተቋማት ላይ ቴህራን ጥቃት አድርሳለች ብላ ከመወንጀሏ ጋር ተያይዞ ነው።

ልዑሉ ከሲቢኤስ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቆይታ በጋዜጠኛው ጀማል ካሾጊ ግድያም ላይም የተወሰነ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ቢናገሩም ለግድያው ትዕዛዝ አልሰጠሁም ሲሉ ክደዋል።

የሳዑዲ አረቢያ መሪ ተደርገው የሚታዩት ልዑሉ በሰላ ትችቱ የሚታወቀውን የሳዑዲ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ በቀጥታ ተሳትፈዋል ተብለውም ይጠረጠራሉ።

ካሾጊ የተገደለው በቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ባለፈው አመት ነው።

የመካካለኛው ምሥራቅ ቀጠና በዓለም ላይ ያለውን 30 በመቶ ነዳጅ አቅራቢ ሲሆን፣ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም አቀፉ ንግድ መተላለፊያ እንዲሁም 4 በመቶ የዓለም ሃገራት አጠቃላይ ምርት ድምርን የሚያበረክት ነው ብለዋል።

"እስቲ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ቀጥ ቢሉ ብላችሁ አስቡ፤ ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ይወድቃል፤ የሚጎዱት ሳዑዲ አረቢያ ወይም የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ብቻ አይሆኑም" ብለዋል።

ሳዑዲ አረቢያ እንደምትለው በ18 ሰው አልባ አውሮፕላኖችና በሰባት ሚሳይሎች አማካኝነት ከሁለት ሳምንታት በፊት በሁለት የነዳጅ ተቋማቷ ላይ ጥቃት እንደደረሰባት ነው።

በኢራን የሚደገፈው የሁቲ አማፅያን ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ መኖራቸውን ቢያሳውቁም ሳዑዲ አረቢያ ግን የዓለም 5 በመቶ ነዳጅ የሚያቀርበውን ስፍራ በማጥቃትና የዓለምን የነዳጅ ዋጋ በማዛባት ኢራንን በመወንጀል ፀንታለች።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ ለዚህ ምላሽ የሚሆን ብዙ አማራጭ እንዳላቸውና "የሚያስገድድ አማራጭ" ሊጠቀሙ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)