የሶሪያው አሌፖ ባብዛኛው በሀገሪቱ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መዋሉ ተጠቆመ

የሶሪያ ብሄራዊ መገናኛ ብዙሃን ጥንታዊቷ አሌፖ (ኦልድ አሌፖ) በሀገሪቱ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መዋሉን ዘግቧል።

የሶርያ ተቃዋሚ ሀይሎች ጥንታዊ ቅርሶች የሚገኙበትን የአሌፖ አካባቢ (ኦልድ አሌፖ) ለቀው መውጣታቸውን ነው የተመለከተው ።

ከበርካታ ቀናት ከባድ ውጊያ በኋላ ነው ተፋላሚ ሃይሎቹ አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ለቀው የወጡት ። 

በአሁኑ ወቅት የመንግስት ወታደሮች ባለፉት አራት አመታት በተቃዋሚ ሀይሎች ስር የነበረውን ምስራቃዊ አሌፖ 75 በመቶውን በቁጥጥር ስር አውለዋል።

የከተማዋ ደቡብ ምስራቅ ክፍሎችን ከተፋላሚ ወገኖች ለማስለቀቅም ውጊያው ቀጥሏል ተብሏል።

ምንም እንኳን አብዛኛው የአሌፖ ግዛት ነፃ ቢወጣም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ተቃዋሚዎች በያዟቸው አካባቢዎች ይገኛሉ ተብሏል።

በዚህም የአሳድ መንግስት ንፁሃኑን ወደ ሌላ አካባቢ የማሸጋገር ሰፊ ስራ መስራት እንዳለበት እየተጠየቀ ነው።

በምስራቃዊ አሌፖም ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት እና የህክምና ተቋማት ችግር አጋጥሟል።

በተቃዋሚ ሀይሎች ስር በሚገኙ አካባቢዎች የሚገኙ ንፁሃን ዜጎችን ለማስወጣትም የአምስት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ቢጠየቅም የሶሪያ መንግስት በአሌፖ ምንም አይነት የተኩስ አቁም ስምምነት አይኖርም ብሏል፡፡

የመንግስት ሀይሎች ትናንት ባደረጉት የቦምብ ድብደባም 15 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።