የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ፓርክ ከስልጣናቸው ታገዱ

የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ፕሬዚዳንት ፓርክ ጊዩን ሀይን ክስ እንዲመሰረትባቸባው የሚያስችል ድምፅ ሰጠ።

በዛሬው እለት ፕሬዚዳንቷ ይከሰሱ ወይስ አይከሰሱ የሚለውን ድምፅ የሰጠው የሀገሪቱ ፓርላማም ፓርክ እንዲከሰሱ ድምፅ ሰጥቷል።

በዚሁም መሰረት የፕሬዚዳንቷን መከሰስ 234 የፓርላማው አባላት ሲደግፉት፤ 56ቱ ተቃውመውታል።

በዚህም መሰረት የሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ፕሬዚዳንት ፓርክ ከስልጣናቸው ታግደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዋንግ ዮ አህን የፓርክን ስልጣን ይረከባሉ ተብሏል።

ፕሬዚዳንት ፓርክ የ40 አመታት ወዳጃቸው ቾይ ሱን ሲል የሀገሪቱን ሚስጥር እንዲያውቁና እና ባልተገባ መንገድ ገንዘብን እንዲያገኙ ረድተዋቸዋል በሚል ነው ችግር ውስጥ የገቡት።

በሙስና የተጠረጠሩት ፓርክ ምንም እንኳን ጉዳዩን ቢያስተባብሉም ከወዳጃቸው ቾይ ጋር ለነበራቸው ጥብቅ ግንኙነት በተደጋጋሚ የሀገሪቱን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንቷ ከሙስና ጋር በተያያዘ መጠርጠራቸውን ተከትሎ በርካታ ደቡብ ኮሪያውያን ወደ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን የገለጹ ሲሆን፤ ከስልጣናቸው እንዲለቁም ጠይቋል።

ከስልጣን በጊዜያዊነት የታገዱት ፓርክ ጉዳይ እልባት የሚያገኘው ግን በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ነው።

የደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት የሆኑት ፓርክ ጊዮን ሀይ ከስልጣናቸው የሚነሱ ከሆነ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው የስልጣን ጊዜያቸው ሳይጠናቀቅ ከሀላፊነታቸው የተነሱ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ።

በስድስት ወራት ውስጥ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንቷን በተጠረጠሩበት ወንጀል ነፃ ናቸው ብሎ ከወሰነ ፕሬዚዳንት ፓርክ በስልጣናቸው የሚቀጥሉ ይሆናል። እስከዚያው ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዋንግ ዮ አህን  ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ሀገሪቱን ይመራሉ-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።