ባለፈው ሳምንት የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርኮል ተርቡል ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመደወል ከመመረጣቸው በፊት በአውስትራሊያ የሚገኙ ስደተኞችን ለመቀበል ተደርጎ የነበረን ስምምነት እንዲያከብሩ የጠየቁ ቢሆንም በአሜሪካ በኩል ተቀባይነት አላገኘም።
ባለፈው ቅዳሜ ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት የስልክ ውይይት አለመግባባት በመፈጠሩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ውይይቱ ሳይጠናቀቅ ስልኩን ማቋረጣቸው ኒዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
በውይይቱ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቀደም ሲል የኦባማ መንግስት 1 ሺህ 240 ስደተኞችን ከአውስትራሊያ ለመቀበል ተስማምቶ እንደነበር ገልጸው አሁን ወደስልጣን የመጣው የአሜሪካ መንግስትም ይህንን ስምምነት እንዲያከብር ነበር የጠየቁት።
እንደዘገባው ከሆነ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንፕ ይህንን ስምምነት እንደማይቀበሉ ገልጸው ውይይቱ ሳይቋጭ ስልኩን በመዝጋታቸው የሁቱ ወዳጅ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሊወድቅ ይችላል ሲል ኒዮርክ ታይምስ ዘግቧል።