የፀጥታው ምክር ቤት በሶሪያ በተፈፀመው የኬሚካል ጥቃት እየመከረ ነው

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሶሪያ በመርዛማ ኬሚካል አማካኝነት ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት በኒውዮርክ ውይይት ማድረግ ጀምሯል።

ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና አሜሪካ በኢድሊብ ግዛት የተፈፀመው ጥቃት በጥልቀት እንዲጣራ ረቂቅ ሀሳብ ማቅረባቸውም ተሰምቷል።

ሩስያ ግን ይህን ሀሳብ አልተቀበለችውም፤ የደማስቆ ዋነኛ አጋዥ መሆኗን በመጥቀስ ረቂቁን ተቀባይነት የሌለው ብላዋለች።

ሶስቱ ሀገራት ያቀረቡት ረቂቅ ሀሳብ ማክሰኞ እለት በሃን ሼክሁን የደረሰውን ጥቃት መንስኤ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች አስወጋጅ ድርጅት እንዲያጣራው ይጠይቃል።

የሶሪያ መንግስት ጥቃቱ በደረሰበት ቀን የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ የተመለከቱ መረጃዎች፣ የውጊያ እቅዶች እና የአውሮፕላን በረራ እንቅስቃሴዎች መረጃ እንዲያቀርብም ነው ይህ ረቂቅ ሀሳብ የሚጠይቀው።

ደማስቆ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች አስወጋጅ ድርጅት አጣሪ ቡድኖች የኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቃት ተፈፅሞበታል የተባለውን ስፍራ እንዲጎበኙ መፍቀድ እንዳለባትም ይጠይቃል። 

ለስድስት አመታት በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በምትገኘው ሶሪያ ኢድሊብ ግዛት በኬሚካል ጦር መሳሪያ ሳይደርስ አልቀረም በተባለው ጥቃት 72 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። 

ከሟቾቹ ውስጥም 20ዎቹ ህፃናት ናቸው።

ንብረትነታቸው የሩስያ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ የሚገመቱ የጦር ጄቶች ባለፈው እሁድ በሰሜናዊ ኢድሊብ ግዛት በሚገኝ ሆስፒታል ላይ ባደረሷቸው ሶስት የአየር ጥቃቶች ቢያንስ 10 ሰዎች መቁሰላቸው እና የሆስፒታሉ ህንጻ መፍረሱን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል-(ኤፍ ቢ ሲ)።