በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ የተፈጸመውንና የደርዘኖቹን ሕይወት የቀጠፈውን የኬሚካል ጋዝ ጥቃት ተከትሎ አሜሪካን የሚሳኤል የጥቃት እርምጃ በሶሪያ መንግስት ላይ ፈጽማለች፡፡
የአሜሪካን ባለስልጣናት እንደገለጹት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጥዕዛዝ ተከትሎ 59 የሚሆኑ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በሶሪያው የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች መገኛ የሆነውን ቦታ እንዳወደሙ ታውቋል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን እንደገለፀው፣ ሚሳኤሎቹ የተወነጨፉት በሜዲትራንያን ባህር ላይ ከሚገኝ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ነው፡፡
የፔንታጎኑ ቃል አቀባይ ካፒቴን ጄፍ ዳቪስ ለዘጋቢዎች እንደተናገሩት ጥቃቱ የተሰነዘረው ትላንት ከምሽቱ 2፡40 እንደሆነና በጥቃቱም አውሮፕላኖች፣ የአውሮፕላን መጠለያዎች፣ ነዳጅ፣ የሎጂስቲክ መጋዝን፣ የአየር መቃወሚያ ሲስተሞች እንደወደሙ ታውቋል፡፡ ጥቃቱ ሶሪያ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች ዳግም እንዳትጠቀም በሚያስችል ደረጃ አውድሞታል፡፡
የአሜሪካን ባለስልጣናት የአሳድ መንግስት የተከለከሉ የጦር መሳሪያ ኬሚካሎችን እንደተጠቀመ ገልጸዋል፡፡
በጥቃቱ ስድስት ወታደሮች መገደላቸውንም ታውቋል፡፡
በማክሰኞው የኬሚካል ጥቃት 26 ሕጻናትን ጨምሮ 86 ንጹሐን ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ይታወሳል፡፡ (ሲኤንኤን)