ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች

ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የዋሽንግተን ድርጊት ፒዮንግያንግ የኒውክሌር ጦር መሳርያን በማምረት ራሷን እንድትከላከል የማድረግ መብት እንዳላት የሚሳይ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡

የሰሜን ኮርያ ጎረቤት የሆኑት ደቡብ ኮርያና ቻይና ፒዮንግያንግ ተጨማሪ የኒውክሌርና የሚሳኤል ሙከራ የምታደርግ ከሆነ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃት ገልፀዋል፡፡ ቅጣቱ ደግሞ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣልን ሊያስከትል እንደሚችል ነው ያስረዱት፡፡

በኮርያ ባህረሰላጤ የቻይና ተወካይ ዉ ዳዌ ከደቡብ ኮርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ከከፍተኛ የኒውክሌር ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

ከሰሜን ኮርያ ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት ያላት ቻይና ከፒዮንግያግ ወደ ቻይና በሚገቡ ሁሉም የከሰል ምርቶች ላይ ከባለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ማዕቀብ ጥላለች፡፡

ደቡብ ኮርያ፣አሜሪካና ጃፓን በሰሜን ኮርያ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችላቸው ጉዳይ ዙርያ ለመምከር በዚህ ወር መጨረሻ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

ፒዮንግያንግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ ከማንኛውም ሙከራ የታገደች ቢሆንም የረጅም ርቀት ሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ መዘጋጀቷን የሚያሳዩ ፍንጮች እየወጡ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ዛሬም በባላንጣነት የሚተያዩት ፒንግያንግና ዋሽንግተን የእሰጣገባውን መድረክ ተቆጣጥረውታል፡፡

ባለፈው ሳምንት ፒንግያንግ ከፀብ አጫሪነት ድርጊቷ እንድትታቀብ ቻይና ከጎኗ እንድትሰለፍ አሜሪካ ጥሪ አቅርባ ነበር፡፡

ቤጂንግ ለዋሽንግተን ጥሪ አጥጋቢ ምላሽ ካልሰጠች አሜሪካ ብቻዋን የበኩሏን እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች፡፡

ይህንንም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው የተላኩ ልዑካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

ጉዳዩ በዚህ ሳያበቃም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ሺ ዥንፒንግ ጋር  በአሜሪካ ተገናኝተው መክረዋል፡፡

የንግድ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር በተጨማሪ በሰሜን ኮርያ ጉዳይም አብረው እንደሚሰሩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

አሜሪካ በኮርያ ባህረሰላጤ የባህር ኃይሏን ለማጠናከር ተጨማሪ ጦር ማስፈሯ ፒዮንግያግን አስቆጥቷል፡፡

የአሜሪካ ድርጊት ግዴለሽነት የሰፈነበት ወረራ ነው ስትልም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል በሰጠችው መግለጫ ዋሽንግተንን ወርፋለች፡፡

የአሜሪካ እርምጃ በፓስፊክ የአሜሪካ ምድብ ጦር የቀጣናውን ኃይል ለማጠናከር የተደረገ ዝግጅት መሆኑ ተነግሯል፡፡

በምድብ ጦሩ ተዋጊ አውሮፕላኖችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች መስፈራቸው ነው የተመለከተው፡፡