በእስራኤል ከ1ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ታሳሪዎች የረሃብ አድማ መቱ

በእስራኤል ማረሚያ ቤት የሚገኙ ከአንድ ሺ በላይ ፍልስጥኤማውያን የረሀብ አድማ መቱ፡፡

የእስራኤል መንግስት ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለጸ ሲሆን አድማውን አስተባብሯል የተባለው  የቀድሞውን የፋታህ መሪ ማርዋን ባጎቲን ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት እንዲዛወር ተድርጓል ብሏል፡፡

በቅርቡ በአንድ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ከአንድ ሺ በላይ ፍልስጥኤማውያን የረሃብ አድማ መተዋል፡፡

ፍልስጤማውያን ታራሚዎቹ እስር ቤቱ ለታራሚዎች ምቹ አለመሆኑን በመቃወም ነው አድማውን እንደመቱ የተገለፀው፡፡

በማረሚያ ቤቱ የሚሠጠው አገልግሎትም ደረጃውን ያልጠበቀና ለታራሚዎች የማይመጥን እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ አሸባሪ ተብለው መታሰራቸውም ለአድማው ሌላኛው ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

አድማውን አስተባብሯል የተባለው ማርዋን ባጎቲን ሀዳሪም ከተባለው ማረሚያ ቤት ወደ ጃላማ ተዛውሮ ለብቻው እንዲታሰር መደረጉን ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል፡፡ የቀድሞው የፋታህ መሪ የነበረው ባጎቲ የታራሚዎቹ መሪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የተወሰኑ እስረኞችም ወደ ሌላ ማረሚያ ቤቶች ተወስደው መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ የረሀብ አድማው የፍልስጥኤም የእስረኞች ቀን እየተባለ በየዓመቱ ሚያዝያ 17 ቀን ከሚከበረው የመታሰቢያ ቀን ጋር እንዲመሳሰል ታስቦ የተደረገ መሆኑም ነው የተመለከተው፡፡

ታራሚዎቹ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ በግልፅ ሊወያይና ሊደራደር እንደሚገባ ጥያቄ ቢያቀርቡም የእስራኤል መንግስት ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል፡፡

የእስራኤል የደህንነት ሚኒስትር ጊላድ ኤርዳን ‹‹ከታራሚዎቹ ጋር ለመደራደር የሚያስገድደን  ምንም ዓይነት ምክንያት የለም›› በማለት የመንግስታቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

የታራሚዎቹን ውሳኔ በመደገፍ በርካታ ፍልስጥኤማውያን በዌስት ባንክ አቅራቢያ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ በዚህም ከእስራኤል ፖሊሶች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በርካታ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ግጭት በመፍጠር በእስራኤል ማረሚያ ቤቶች ለእሥር የታዳረጉ ሲሆን በእስራኤል ማረሚያ ቤት ከስድስት ሺ በላይ ታራሚዎች እንዳሉ ይገለፃል፡፡