ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ብሄራዊ ምርጫ ሩሲያ ጣልቃ መግባቷን ተቀበሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ሩሲያ በ2016 የአሜሪካ ብሄራዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች ሲሉ የደረሱበትን ድምዳሜ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡

ሀሳባቸውን በመቀያየር የሚታወቁት አወዛጋቢው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት የ2016ቱን የአሜሪካ ምርጫ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ሩሲያ እጇን አስገብታለች ብለው ደምድመዋል፡፡

ይህን የደንነት ተቋማት ድምዳሜ ተከትሎ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በአሜሪካ የሚገኙ የሩሲያ ዲፕሎማቶች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ሲያደርግ ከዋሽንግተን ውጪ የሚገኙ ሁለት የሩሲያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን መዝጋቱ አይዘነጋም፡፡

ያም ቢሆን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመሩበት ወቅት አንስቶ የተቋማቱ ድምዳሜ ተራ ውንጀላ ነው ሲሉ ሰንብተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን ቢሉም  የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች እና የደህንነት ተቋማት ጉዳዩን ለማጣራት ከላይ ታች ሲማስኑ ቆይተዋል፡፡

በቀድሞው የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ሀላፊ ሮበርት ሙለር የሚመራው የምርመራ ቡድንም በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው አለበት ያላቸውን አካላት በመመርመር ወደ ሁለት ደርዘን የሚጠጉ አሜሪካውያን እና ሩሲያውያን ላይ ክስ መመስረቱ ይታወቃል፡፡

የሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ ገብታለች የሚለው ሀሳብ ሚዛን እየደፋ ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ከሰሞኑ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ካወሩ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት የደረሱበትን ድምዳሜ እንደማይቀቡሉ ገልጸዋል፡፡

ይህን በተናገሩ በሰአታት ልዩነት ውስጥ ሀሳባቸውን ቀይረው የአሜሪካ ደህንነት ተቋማት ድምዳሜን ተከትሎ የተመሰረተውን ክስ ተቀብያለሁ ማለታቸውን የመገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ትራምፕ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በሄልሲንኪ ካገኙ በኋላ ሰኞ እለት የተናገሩት የመጀመሪያው አስተያየታቸው ጠንከር ያሉ ትችቶችን ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡

ታዲያ ፕሬዚደንት ትራምፕ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኃላ በሰጡት ማብራሪያ መግለጫውን በሚሰጡበት ወቅት የንባብ ስህተት መስራታቸውን አምነዋል፡፡

ሩሲያ ጣልቃ አለመግባቷን የሚያሳይ ምንም አላየሁም የሚለውን አረፍተ ነገር ሩሲያ በምርጫው ጣልቃ መግባቷን የሚያሳይ ምንም አላየሁም በሚል በማንበቤ ምክንያት የተፈጠረ ስህተት ነው ብለዋል ፕሬዚደንቱ፡፡

ያም ሆነ ይህ የቢቢሲው ተንታኝ አንቶኒ ዙርከር በሰጠው አስተያየት ፕሬዝዳንቱ የአፍ ወለምታ ነው ሲሉ የገለጹትን ንግግር ለማመን የሚያስቸግር ደካማ ምክንያት ነው ይላል፡፡

የእሳቸው ቀንደኛ ደጋፊዎች እንኳን ሳይቀሩ ትራምፕ መወላወላቸውን ትተው ትክክለኛውን አቋማቸውን እንዲያስታውቁ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

የሪፐብሊካን እና የዴሞክራት ፖለቲከኞች እንዲሁም የደህንነት መስሪያ ቤት ባለሙያዎች ትራምፕ ከፑቲን ጋር የሰጡት መግለጫ እጅግ ተገቢነት የጎደለው እና አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ እንዴት ከሀገራቸው ተቋማት ድምዳሜ ይበልጥ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ሊያምኑ ቻሉ የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡

ባስ ሲልም የዲሞክራት ፖለቲከኞች ትራምፕ በሀገር ክህደት ወንጀል ሊጠየቁ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡   

ፕሬዝዳንቱ በሰጡት አዲሱ አስተያየታቸው ለአሜሪካው የደህንነት ኤጀንሲ ሙሉ እምነትና ድጋፍ አለኝ ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ብሄራዊ ምርጫ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ጠቅሰው በምርጫው ውጤት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የለውም ብለዋል፡፡ የምርጫ ዘመቻ ቡድናቸውም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለመሳተፉን ገልጸዋል፡፡

ትራምፕ ከፑቲን ጋር በነበራቸው ቆይታ መገናኛ ብዙኀን የተዛቡ መረጃዎችን አቅርበዋል ሲሉም ተችተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህን ቢሉም የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት በድምዳሜያቸው እንደሚጸኑ ፕሬዝዳንቱ የሰጡትን አስተያየት ተከትለው ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በሮበርት ሙለር የሚመራው አጣሪ ብድንም ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡