የእስራኤል ፓርላማ የአገሪቱ መንግሥት አይሁድ ላይ የተመሠረተ ነው የሚለውን ሰነድ አፀደቀ

የእስራኤል ፓርላማ ያፀደቀው ሰነድ የሀገሪቱ መንግስት በጀውሽ ላይ የተመሰረተ መንግስት ነው የሚለው ነው፡፡ 

ጥንታዊት ሀገር እስራኤል ከዓለም ካርታ እስከ መጥፋት የደረሰችበትን ወቅት ተሻግራ ዳግም እንደ ሀገር ከተመሰረተች ወዲህ የ70ኛ ዓመት የልደት ሻማዋን ካበራችው ገና ወራት ብቻ ተቆጥረዋል፡፡

እስራኤል በ70 ዓመት የልደት በዓሏ ኢየሩሳሌምን የሀገሯ ርዕሰ መዲና ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ከአሜሪካው የወቅቱ አስተዳደር ጋር በመሆን የአሜሪካ ኤምባሲን ከቴላቪቭ ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ኢየሩሳለም ያዘዋወረችበት ተግባሯ ይጠቀሳል፡፡

ይህን ተከትሎ የተወሰኑ ሀገራት ኤምባሲያቸውን ወደ ኢየሩሳለም በማዘዋወር ለከተማዋ የእስራኤል መዲናነት እውቅናቸውን ችረዋል፡፡ በዚህም ከበርካታ የዓረቡ ዓለም ሀገራት በተለይም ተግባሩ ህልውናዬን ይፈታተናል ከምትለው ፊሊስጤም ሰፊ ውዝግብ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ 

አሁን ደግሞ እስራኤል ከዓረቡ ዓለም ጋር ይበልጥ የሚያቃቅራትን ውሳኔ በህዝብ እንደራሴዋ በኩል ማስተላለፏ ተሰምቷል፡፡

እስራኤል የይሁዳ ምድር በመሆኗ የአይሁድ ህዝብ ብቻ ሀገር ናት የሚያስብለውን ውሳኔ ጀውሽ ኔሽን ስቴት ቢል የተሰኘውን ሰነድ ለፓርላማዋ በማቅረብ ለተግባራዊነቱም ማጽደቋ ነው፡፡

ይህ የጀውሽ ኔሽን ስቴት ቢል ወይም የይሁዳ መንግስት ሰነድ ከሚያስከትላቸው ተግባራት አንዱ የአረብኛ ቋንቋን ከብሔራዊ ቋንቋነት ማውረድና የጀውሽ ሰፈራን የብሔራዊ ፍላጎት አድርጎ ማሳደግ ነው፡፡ በዚህ ሰነድ መሰረት መላው እና የተቀናጀች ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ትሆናለች፡፡

በእስራኤል ህዝብ እንደራሴዎች የአረቡ ህዝብ ተወካዮች ሰነዱን አጥብቀው ብቃወሙትም የኢስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የሰነዱን መጽደቅ ወቅቱን የጠበቀ በሚል ገልጸውታል፡፡

በሀገሪቱ ቀኝ ዘመም ፓርቲና በአሁን ወቅት እስራኤልን እያስተዳደረ በሚገኘው መንግስት ሰነዱ የጀውሽ ታሪካዊ ስፍራ የሆነችው እስራኤል ላይ የሀገር ባለቤትነትና የእራስን እጣፈንታ በራስ የመወሰን ጉዳይን ለጀውሽ ህዝብ የሚሰጥ በመሆኑ ተገቢ ነው የሚል አቋምም አላቸው፡፡

ሰነዱ በእስራኤሉ ፓርላማ ፊት ቀርቦ 8 ሰዓታትን በፈጀው እልህ አስጨራሽ ክርክር ነው 62 የድጋፍ ድምጾችን አግኝቶ የጸደቀው፡፡ 55 ድምጽ የሰጡ የፓርላማው አባላት ሰነዱን ብቃወሙም በጥቂት ድምጽ ተበልጠው ሳይሳካላቸው ቀርተዋል፡፡

በፓርላማው ክርክር እስራኤል የምትሆነው ለይሁዳ ህዝብ ብቻ ነው የሚሉ እና መሰል መልእክት ያላቸው አንቀጾች እንዲቀነሱ ተደርጓል፡፡ በአሁን ወቅት እስራኤል ውስጥ ከሚኖሩ 9 ሚሊየን እስራኤላውያን 20 ከመቶው የአረብ ዝርያ ያላቸው ዜጎች ስለመሆናቸው ነው የሚነገረው፡፡

እነዚህ ዜጎች በሀገሪቱ እንደ ሁሌተኛ ዜጋ እንድንቆጠር ያደርገናል የሚሉትን ሰነድ የተቹት እስካሁን ባሉት ሁኔታዎችም በሀገሪቱ የትምህርት፣ የጤና እና የመኖሪያ ቤት አደላደል ላይ አድሎ መኖሩን ነው የሚነሱት፡፡

በፓርላማው የአረብ ተወካይ የሆነው አህመድ ቲቢ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለምልልስ ሰነዱ በእስራኤል የዴሞክራሲን ሞት ያቀርባል ነው ያሉት፡፡ ለአረብ መብት የሚሟገተው መንግስታዊ ያልሆነ አዳላህ ተቋም በበኩሉ ረቂቅ ህጉ የይሁዳ ብሄር የበላይነትን በማወጅ የዘረኝነት ፖሊሲዎችን እያስፋፋ ይገኛል ብሏል፡፡

ህጉን የተከላከሉት የኢስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ብዙሃኑ ውሳኔ የማስተላለፍ መብት ብኖራቸውም የአናሳዎች መብትም ይጠበቃል ነው ያሉት ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡