ሰሜን ኮርያ አዲስ የባሊስቲክ ሚሳኤል ግንባታ እያከናወነች እንደሆነ የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታወቁ

ሰሜን ኮርያ አዲስ የባሊስቲክ ሚሳኤል ግንባታ እያከናወነች እንደሆነ የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ሀገሪቱ ከአለም ያቆራረጣትን የኒዉክለር ግንባታ ለመግታት ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካ አቻቸዉ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባለፈዉ የፈረንጆቹ ሰኔ 12 በሲንጋፖር መስማማታቸዉ ይታወሳል።

ሰኞ እለት የወጣዉ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ያስነበበዉ ፅሁፍም ሰሜን ኮርያ አንድ ወይም ሁለት የሚሆኑ አዳዲስ በፈሳሽ የተሞሉ አህጉር አቋራጭ የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን መገንባት ስለመጀመሯ ያትታል።

ሰሜን ኮርያ ከአስከፊዉ የ1950ዎቹ መጀመሪያ የኮርያ ልሳነ ምድር ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ከቀሪዉ አለም ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ቅጥ አጥቶ ለአመታት ተነጥላ ቆይታለች።

ታዲያ አምባገነናዊ በሆነዉና የአንድ ቤተሰብ አባላት ብቻ ለአመታት በተፈራረቁበት የሀገሪቱ የስልጣን ታሪክ የነኪም ቤተሰቦች ከሰላም ይልቅ ጠብን፣ ከዲፕሎማሲ ይልቅ ጦርነትን ምርጫቸዉ አድርገዉ ከጎረቤት ደቡብ ኮርያም ሆነ ከሌሎች የአለም ሀገራት ጋር በክፉ አይን ሲተያየዩ ኖረዋል።

ሀገሪቱ የተጠመደችበት የኒዉክለር ግንባታ ሂደት ታዲያ ዲፕሎማሲዋን አፈር ያበላና በተለይም ከምዕራባዊያኑ ጋር ያላትን ግንኙነት ይባሱኑ ያሻከረ ሆኗል። በዚህም በሰሜን ኮርያና በምዕራባዊያኑ በተለይም ከአሜሪካ ጋር ዘለግ ያሉ የፍጥጫና የስጋት አመታት ተቆጥረዋል።

ሆኖም የሰኔ 12ቱ የሲንጋፖር ስምምነት ሰሜን ኮርያ ለአመታት ችክ ያለችበትን የትንኮሳ አቋም ወደ ማለዘቡ ስለመምጣቷ ያመላከተ ሆኖ ቆይቷል። አለምም ቢሆን ሂደቱን በብርቱ ማወደሱ ይታወቃል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት አሁን ይፋ ያደረጉት መረጃ ግን የኮርያ ልሳነ ምድር ወደ ሰላም ሊመጣ ነዉ የሚለዉን የተስፋ ግንብ እንዳይንደዉ ተሰግቷል። ከአሜሪካ ጋር የተጀመረዉን የሰላም ሂደትም እንዲሁ።

ሰኞ እለት የወጣዉ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ያስነበበዉ ፅሁፍም ሰሜን ኮርያ አንድ ወይም ሁለት የሚሆኑ አዳዲስ በፈሳሽ የተሞሉ አህጉር አቋራጭ የባሊስቲክ ሚሳኤሎችን መገንባት ስለመጀመሯ ያትታል።

ግንባታዉም በሀገሪቱ መዲና ፒዮንግያንግ አቅራቢያ በሚገኘዉ የሳኑምዶንግ ጣቢያ እየተካሄደ ስለመሆኑም መረጃ ያነሳል፡፡

የአሜሪካ ባለስልጣናት እንዳሉት በፈሳሽ ተሞልቷል የተባለዉ ሚሳኤል በጠጣር ቁሶች ከተሞላዉ አንፃር ሲታይ ብዙም አስጊ አለመሆኑ ታዉቋል።

አሁን የወጣዉ መረጃ ሰሜን ኮርያ አሁንም ድረስ ከተለመደ ተግባሯ አለመቆጠቧንና ለሲንጋፖሩ ስምምነትም ተገዢ አለመሆኗን የሚያሳይ ነዉ የሚሉም በርክተዋል።

በሰኔ 12ቱ የሲንጋፖሩ ስምምነት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮርያ አቻቸዉ ኪም ጆንግ ኡን የኮርያን ልሳነ ምድር ፍፁም ከኒዉክለር ነፃ ለማድረግ መስማማታቸዉ የሚታወስ ቢሆንም፤ ከኒዉክለር ነፃ መሆን የሚለዉ ሀሳብ በሁለቱም ወገኖች በኩል ግልፅ ማብራሪያ አለማግኘቱ ጉዳዩን አወሳስቦታል።

ከዚያም ባለፈ እዉን ሰሜን ኮርያ የተባለዉን የጦር መሳሪያ ቅነሳ ቁርጠኛ ሆና ተግባራዊ ታደርገዋለች የሚለዉ ጉዳይ በርካቶቹን የዘርፉን ባለሙያዎች ጥርጣሬ ዉስጥ ከቷል ሲል የዘገበዉ ቢቢሲ ነዉ።