ብሪታኒያ የሩሲያ ደህንነት መስሪያ ቤት የመረጃ ስርቆትና ማመሰቃቀል ወንጀል ፈፀሞብኛል ስትል ከሰሰች

ብሪታኒያ የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የመረጃ ስርቆትና ማመሰቃቀል ወንጀል ፈፀሞብኛል ስትል ክስ አቅርባለች፡፡

ብሪታኒያ እና ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አለመግባባት ውስጥ መግባት ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የቀድሞው የሩሲያ ወታደራዊ ክፍል ኃላፊና የአሁኑ የብሪታኒያ ደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኛ በሆነው ሰርጌ ሰከሪፓል እና ልጁን ዩሊያ እስክሪፓልን ሩሲያ የአምዕሮ ነርቭ መመረዝ ጥቃት አድርሳለች በማለት ብሪታኒያ ክስ ማቅረቧ እና ጉዳዮ ወደ መካረር መሄዱ ይታወሳል፡፡

አሁን ደግሞ የብሪታኒያ መንግስት የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት በሀገሪቱ አራት ዋና ዋና መስሪያ ቤቶች ላይ የመረጃ ማመሰቃቀል እና ስርቆት አካሂዷል ሲል ክስ ማቅረቡን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

የብሪታኒያ ብሄራዊ የመረጃ ደህንነት ማዕከል እንዳለው ከሆነ ደግሞ ጥቃቱ በአብዛኛው አላማ ያደረገው በሩሲያ እና ዩክሬን  በሚገኙ የብሪታኒያ ድርጅቶች ላይ ሲሆን በብሪታኒያ ውስጥ በሚገኙ ጥቂት ተቋማት ላይም መረጃ ስርቆት እንደተደረገ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ሩሲያ በሀገሪቱ በሚገኙ የተወሰኑ የጸረ አበረታች ድርጅት ኮምፒዩተሮች ላይም የሳይበር ጥቃት እንደፈፀመች ብሪታኒያ አስታውቃለች፡፡

በብሪታኒያ የሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ባለሙያ የሆኑት ሰር ብራድሊ ዊግንስ እና ክሪስ ፍሮም የመረጃ ስርቆት ጥቃቱ ከተካሄደ በኋላ ባደረጉት ማጣራት ጥቃቱን የፈፀመው የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት እንደሆነ የሚያሳይ ፍንጭ አግኝተናል ሲሉ ነው የገለፁት፡፡

የብሪታኒያ ብሄራዊ መረጃ ደህንነት ማዕከልም ከዚህ ምርመራ በኋላ በእርግጠኝነት ለዚህ የመርጃ ስርቆት ጥቃት ሩሲያ ኃላፊነት ትወስዳለች ሲል አስታውቋል፡፡

የመረጃ ደህንነት መስሪያ ቤቱ አያይዞም ሩሲያ ጥቃቱን ለመፈጸም በበርካታ ሰዎች ስም አካውንት በመክፈት ሲሆን በአለም የፀረ አበረታች መስሪያ ቤት ላይ የዳታ ቤዝ ማመሰቃቀል በመፈፀም፣ በዩክሬን የአየር መንገድ እና በብሪታኒያ ተቋማት ላይ የኢሜል እና አካውንት ስርቆት በመፈጸም ወንጀል መረጃዎች እንዲመሰቃቀሉ አድርጋለች በዚህም ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡

የብሪታኒያ መንግስት ድርጊቱን ህገ ወጥነትና ግዴለሽነት የተሞላው ሲሆን በሌላ ሀገራት ምርጫዎች ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ ነው ይህ ደግሞ ሩሲያን ዜጎችም ይሁን ኩባንያዎች ይጎዳል ነው ያለው፡፡

ይህንን የመረጃ ስርቆትና ማመሰቃቀል ወንጀል የፈፀመው የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ግን በህግ ተጠያቂ የማደረጉ ስራ ይቀጥላል ሲሉ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚይ ሃንት ለቢቢሲ ገልፀዋል፡፡