በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እጃቸውን ያሰገቡ ተፋላሚ ሀይሎች ጦርነት እንዲያቆሙ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እጃቸውን ያሰገቡ ተፋላሚ ሀይሎች ጦርነት እንዲያቆሙ እና በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በየመን ከአውሮፓውያኑ 2015 መጀመሪያዎቹ ላይ የሁቲ አማጺያን አብዛኛውን የሀገሪቱን ምእራባዊ ክፍል በመቆጣጠር በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት አብድራቡህ መንሱር ሃዲ ከሀገር እንዲኮበልሉ ማድረጋቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት የመን ቀውስ ውስጥ መዘፈቋ ይታወቃል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ግጭቱ ለአስር ሺህ ዜጎች ህልፈት ምክኒያት ሲሆን ከ55 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ለተለያዩ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከ22 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ለከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ተዳርገዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ሌሎች ሰባት የአረብ ሀገራት የሀገሪቱን መንግስት ዳግም ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ያም ቢሆን አሁን ድረስ በየመን እየታየ ላለው ቀውስ አንዳች መፍትሄ ለማምጣት አልቻሉም፡፡

ይህ የእርስ በእርስ ግጭት እልባት እንዲያገኝ በማሰብ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሆኑት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጂም ማቲስ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ  ተፋላሚ ሀይሎች ጦርነት እንዲያቆሙ እና በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሜሪካ ጉዳዩን በቅርበት ስትከታተል መቆየቷን ያወሱት መከላከያ ሚኒስትሩ ጂም ማቲስ በእርስ በእርስ ግጭቱ እየተሳተፉ ያሉ ሀይሎችም በ30 ቀናት ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በመድረስ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በፍጥነት በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይም ወደፊት መጓዝ አለብን ያሉት ጂም ማቲስ በቀጣይ 3 ቀናት ውስጥ ተጨባጭ ስራ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም  በሚቀጥለው ወር ሁሉም የግጭቱ ሀይሎች በቀጣዩ የፈረንጆቹ ወር ከተባበሩት መንግስታት ልዩ ልዑክ ማርቲን ግሪፍትስ ጋር በስዊድን ተገናኝተው ወደ መፍትሄ ሀሳብ እንዲመጡ አሜሪካ ማሳሰቧን ጠቁመዋል፡፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በበኩላቸው የእርስ በእርስ ግጭቱን ለመግታት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት የሚከናወነው ድርድር በሚቀጥለው ወር መቀጠል ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ማይክ ፖምፒዮ አክለውም ሳዑዲ መራሹ ሀይል በየመን የሚያደርገውን የአየር ላይ ጥቃት እንዲያቆም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የሀውቲ አማጺያንም ወደ ሳኡዲ የሚያስወነጭፉትን ሚሳኤል እንዲያቆሙ አሳስበዋል፡፡

ይህን ጦርነት ለማስቆም ጊዜው አሁን ነው ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጦርነቱን ወደ ስምምነት በመቀየር የመናውያን የሰላም አየር እንዲተነፍሱና ሀገሪቱን ዳግም እንዲገነቡ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ወር የሚደረገው ስብሰባም የግጭቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት በራስ የመተማመን ዘዴዎችን መገንባት፣ ድንበሮችን ከጦር መሳሪያዎች ማጽዳት እና የትላልቅ የጦር መሳሪያዎች ትግበራ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ምልከታዎች ውስጥ እንዲሆን ማድረግን አላማው እንዳደረገ ጠቁመዋል፡፡

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሃውቲ ኃይሎችን በመቃወም የሳዑዲ መራሹን ኃይል የሚደግፍ ሲሆን ኃይሉ በየመን እስከአሁን በፈጸመው የአየር ጥቃትም ትችት እየተሰነዘረበት ይገኛል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት የእርስ በርስ ጦርነቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የመን ዓለም በ100 ዓመታት ውስጥ አይቶት የማያውቀውን የሰብአዊ ቀውስ ልታስተናግድ እንደምትችል ተንብየዋል፡፡ (ምንጭ፡- ቢቢሲ እና አልጀዚራ)