በእንግሊዝ ያሉ አጭበርባሪ ባለሀብቶች ቪዛ ሊከለከሉ ነው

በእንግሊዝ ያሉ አጭበርባሪ ባለሀብቶች ቪዛ ሊከለከሉ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

የእንግሊዝ መንግስት ለከፍተኛ ባለሀብቶች ቪዛን በፍጥነት የሚያድልበት መንገድ የተሳለጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ መሆኑ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ባለሀብቶች በህገወጥ ስራ እንዲሰማሩ በማድረጉ እንደ አዲስ አሰራሩ ሊጤን ይገባል ተብሏል፡፡

በባለሀብት ስም ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ እና የመኖሪያ ፍቃድ የሚያገኙ የዉጭ ሀገር ዜጎች ገንዘብ በማሸሽና ገንዘብን ህጋዊ ለማድረግ የሚሞክሩ ናቸዉ ተብሎ በመጠርጠሩ መሆኑም ተነግሯል፡፡

እስከዛሬ ሲሠራበት የነበረው የቪዛ አሰጣጥ 2 ሚሊዮን ፓውንድና ከዚያ በላይ የሚያሳዩ ባለሀብቶች በተለየ ፍጥነት ቪዛና ሌሎች በእንግሊዝ የመኖር የተመቻቹ ሁኔታዎች እንዲሰናዱላቸው የሚያደርግ ነበር።

ምድብ አንድ በመባል የሚታወቀው ኢንቨስተር ቪዛ ሥራ ላይ የዋለው ከ2008 ጀምሮ ሲሆን ዓላማው ከአውሮፓ ውጭ ያሉ ታላላቅ ባለሐብቶች ንዋያቸውን በእንግሊዝ ምድር እንዲያፈሱ የሚያደርግ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

በዚህ አሰራር ከፍ ያለ ገንዘብ ሂሳባቸው ላይ ማሳየት የቻሉ ባለሐብቶች በፍጥነት ወደ እንግሊዝ እንዲገቡና ከአምስት ዓመት በኋላም በቋሚነት እንዲኖሩ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን አሁን ግን ይህ አሰራር በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ የማድረግ አንድ ስልት ተደርጎ በመወሰዱና በተጨባጭ ለሥራ ፈጠራ እየሰጠ ያለው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ለጊዜው እንዲቆምና ዳግም እንዲጤን ተወስኗል።

የእንግሊዝ የኢሚግሬሽን ሚኒስቴር ካሮላይን ኖክስ ከዚህ በኋላ ቪዛዉን ለግል ጥቅማቸዉ የሚያዉሉ ባለሀብቶችን እንደማይታገሱ ተናግረዉ ህግ እና ስራዓትም ሊከበር ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ሀቀኛ ባለሐብቶች ብቻ ዕድሉን እንዲጠቀሙ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ  እንግሊዝ ውስጥ ገብተው ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚችሉ ሐቀኛ ባለሐብቶች ብቻ  ናቸዉ  አሰራሩም  ከመጪው አርብ ጀምሮ ኦዲት እስከሚደረግ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡

አመልካቾች ይጠየቁ ከነበሩ መመዘኛዎች መካከል በእንግሊዝ ባንክ ጠቀም ያለ የገንዘብ መጠን ማስቀመጥና "መልካም ባህሪ" የተላበሱ መሆን ነው። አመልካቾት መመዘኛዎችን ሲያሟሉ ያለ ተጨማሪ እንግልት የ2 ዓመት ከ4 ወር ቪዛ ሲሰጣቸው ቆይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ቪዛ ማራዘም ሲፈልጉ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ይደረግ ነበር።

በ2017 ብቻ ምድብ አንድ በመጠቀም አንድ ሺህ የሚሆኑ ባለሐብቶች ወደ እንግሊዝ ገብተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የሩሲያና የቻይና ባለሀብቶች በርካታ ናቸዉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡