በፈረንሳይ የተቀሰቀሰውን አመጽ ተከትሎ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ አቀረቡ

በፈረንሳይ ተቀጣጥሎ የቀጠለውን የቢጫ ሰደሪያ አመጽ ተከትሎ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ አቀረቡ፡፡

በምዕራብ አውሮፓዊት ሀገር ፈረንሳይ የኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር ለከባቢያዊ የአየር ለውጥ መፍትሄ ይሆናል በሚል በነዳጅ ላይ የጣሉትን ተጨማሪ ታክስ ተከትሎ በሀገሪቷ ለሳምንታት እየተደረገ ያለው የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት አመጽ በዚህኛው ሳምንትም ተጠናክሮ ነው የቀጠለው፡፡

የብጫ ሰደሪያዎቹ አመጽ ለማለት Yellow vest protests የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ አመጽ በዚህኛው ሳምንት ቅዳሜ ለተከታታይ 4ኛ ሳምንት ነው የተካሄደው፡፡

የፈረንሳይ አብይ የገቢ ምንጭ የሆነውን የቱሪስት ሳይቶች እና በፓሪስ ግዙፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የገበያ ማዕከላትን አዘግቶ የዋለው የዚህኛው ሳምንት የፈረንሳይ አመጽ ከሳምንት ሳምንት ተጠናክሮ በመምጣቱ እና በዚህኛው ሳምንት ቁጥራቸው ካለፉት ሳምንትት የላቁ አማጽያንን በማስተናገዱ በርካቶች ዘብጥያ መውረዳቸውም ነው የተሰማው፡፡

ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ፊሊፕ የሀገሪቱን ብሄራዊ አንድነት መመለስ ይጠበቅብናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፈረንሳይ የነዳጅ ጭማሪን የሚፈቅድ ህግ መውጣቱ የዋጋ ግሽበትን አጧጡፎ የኑሮ ውድነትን አስከትሎብናል ያሉ ፈረንሳውያኑ በዚህም ሳምንት መጨረሻ ቁትራቸው የበዛ የተቃውሞ ሰልፈኞች አደባበባይ በመውጣታቸው የሀገሪቱ ፖሊስ አስለቃሽ ጥስን ተጠቅሞ በትኖአቸዋል፡፡

በዚህኛው ሳምንት ከተሳተፉ አንድ ሺዎቹ ዘብጥያ መውረዳቸው የተሰማ ሲሆን የሀገሪቱ ጠ/ሚ ሰላማዊ የጥያቄ ስልት እና ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር Édouard Philippe አክለው እንደገለጹትም የትኛውም አይነት የታክስ ጭማሪ ሃገራዊ አንድነታችን ሊፈታተን አይገባውም፣ ብሄራዊ አንድነታችንን በውይይት፣ በስራ እና በህብረት እንገነባዋለን ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት ጥሪ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለውይይት ክፍት የሆኑ ሁኔታዎችን እያመቻቹ ይገኛሉ ብለዋልም፡፡

የፈረንሳይ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ክርስቶፍ ካስታነር ሃይልን ተጠቅሞ ሁከቱን በቁጥጥር ስር ያዋለውን የሀገሪቱን ፖሊስ አመስግነዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም የጸጥታ ሃይላቸው ሙያዊ ሃላፊነቱን በመወጣቱ ምስጋናቸውን ችረውአቸዋል፡፡

እንደ የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ገለጻ ከሆነ ከ125ሺህ ህዝብ የበለጡ በአሁኑ ሳምንት መጨረሻ አመጽ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ አመጹን ለመቆጣጠር በግዳጅ ላይ የተሰማሩ የጽጥታ አካላት ደግሞ 90 ሺ ናቸው፡፡ በፓሪስ ብቻ 12 በሙሉ ትጥቅ የታጀቡ ተሸከርካሪዎች እና  8 ሺህ የፖሊስ ሰራተኞች ተሰማርተዋል፡፡

በፓሪስ አደባባይ ወጥተው መስታወቶችን በመሰባበር፣ ተሸከርካሪዎችንም በማውደም ተግባር በመሰማራ የከፋውን አደጋ ያደረሱ የአመጹ ሰልፈኞች በ10ሺህ የሚቆጠሩ ናቸው ተብሏል፡፡ በዚሁ በመዲናዋ ፓሪስ በተካሄደው አመጽ 70 የሚጠጉ የፖሊስ ኦፊሰሮች ቀላል እና ከባድ ጉዳት ማስተናገዳቸውም ተሰምቷል፡፡

ፈረንሳይ የዚህ አይነት የተቃውሞ አመጾችን ከአስርት ዓመታት ወዲህ ስታስተናግድም የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን አሁን አንድ ነገር ይጠበቃል፡፡ እሱም በቀጣይ የሃገሪቱ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ምን ሊሆን ይችላል የሚል፡፡ አማጺያኑ የሚያነሱትን ጥያቄ በቀጥታ መመለስ ወይስ መንግስት በአቋሙ ጸንቶ መቀጠል፡፡ ለዚህ ጥያቄ የኢማኑኤል ማክሮን መንግስት በዚህ ሳምንት የሚሰጠው መልስ ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡ ዘገባውን ለማጠናቀር ቢቢሲና አልጀዚራን  ተጠቀምን ፡፡