ታይም መጽሔት ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊን የዓመቱ ምርጥ በማለት መረጠው

ታዋቂው ታይም መፅሄት የሳውዲ ጋዜጠኛና የቀድሞዉን የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ አምደኛ የሆነውን  ጀማል ካሾጊን የአመቱ ምርጥ ሰዉ ሲል መረጠው ።

በዚህም ካሾጊ በህይወት ካለፈ በኋላ ለዚህ ምርጫ የበቃ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል ተብሏል። ከካሾጊ በተጨማሪ የማያንማር፣ የፊሊፒንስና የሳውዲ አረቢያ ጋዜጠኞችን ጨምሮ አንድ የአሜሪካ ጋዜጣም ለእውነት የቆሙ ዘቦች የሚል ስያሜን አግኝተዋል።

የሳውዲ ንጉሳዊያን ቤተሰቦችን ክፉኛ በመተቸት የሚታወቀዉ የሳዉዲ አረቢያዉ ፀሀፊ ጀማል ካሾጌ ባለፈዉ መስከረም 22 በኢስታንቡል በሚገኘዉ የሳዉዲ አረቢያ ቆንስላ ፅ/ቤት እንደገባ መቅረቱ የአለም መነጋገሪያ ከመሆኑም ባለፈ የበርካታ ሀገራትን ትኩረት ስቦ ዛሬም ድረስ ሀገራትን በሓሳብ የከፈለ ሆኖ ዘልቋል።

የአለም ፖለቲካ መነጋሪያ የሆነው የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ጉዳይ ዛሬም ከመነጋሪያነቱ የራቀ አይመስልም። እውቁ ታይም መፅሄት በየአመቱ በሚያወጣው የአመቱ ምርጥ ሰዉ በዘንድሮዉ ምርጫ ለሙያዉ ሲል የሞተዉን ጋዜጠኛና ጸሃፊ ጃማል ካሾጊን ባለተራ አድርጎታል። በዚህም ካሾጊ በህይወት ካለፈ በኋላ የታይም መፅሄት የአመቱ ምርጥ የተባለ የመጀመሪያው ሰው ስለመሆኑም ተነግሯል።

የታይም መጽሄት ከፍተኛ አርታኢ የሆነዉ ኤድዋርድ ኤልሴንታል  ባለፈዉ መስከረም ወር ላይ በቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘዉ የሳውዲ ኢምባሲ ውስጥ በሳውዲ መንግስት ሴራ የተገደለዉን  ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊን  የዓመቱ ምርጥ ሰው አድርጎ መርጧል ።

በማያናማር የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማጋለጣቸዉ ለእስር የተዳረጉት ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞች፣ ዋ ሎን እና ክያዉ ሶኦ፣ የፍሊፒንሷ ጋዜጠኛ ማሪያ ሬሳ እና መቀመጫዉን በአሜሪካ ያደረገዉ ዘ ካፒታል ጋዜት የዚህ አመት ምርጦች ለመሆንም  ችለዋል።

ታይም መፅሄት የእውነት ዘቦቹና በእውነት ላይ የተከፈተዉ ጦርነት የሚል ርዕስ በሠጠው ጽሑፉ እስካለፈው ሰኞ ብቻ 52 ጋዜጠኖች በዚህ አመት መገደላቸውን ከትቧል።

እናም ካሾጊና መሸሎቹ ከየአቅጣጫዉ የተከፈተባቸዉን ጦርነት ተቋቁመዉ፣ ሲብስም መስዋዕት ሆነው ለመላው አለም መረጃም የሚያካፍሉ ድንቆች ናቸውና ክብር ይገባቸዋል ሲል ለጋዜጠኞቹ ያለዉን አክብሮትና አድናቆት አስፍሯል።  

በዚህም የዘንድሮውን ምርጫ ያሸነፉት ጋዜጠኞች በአራት የተለያዩ የታይም መጽሔት የሽፋን ገፅ ላይ እንደሚታተሙ ተነግሯል።

ጋዜጠኖቹ እውነትን ፍለጋ ብዙ በደል የደረሰባቸው መሆኑና ከፍተኛ መሰዋዕትነትም መክፈላቸው ለመመረጣቸው ምክንያት ነው ተብሏል።

ለአብነትም የአሜሪካው ዘ ካፒታል ጋዜት፣ አንድ ግለሰብ በድንገት በተቋሙ መሥሪያ ቤት ላይ በከፈተዉ የእሩምታ ተኩስ አራት ጋዜጠኞቹና አንድ የሽያጭ ባለሙያው መሞታቸዉ ይነገራል።

ሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞችም በማይናማር በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ምርመራ ሲያካሂዱ ተይዘዉ ለአንድ አመት ያክል ዘብጥያ ወርደዋል።

የፊሊፒንሷ ተሸላሚ ጋዜጠኛ ማሪያ ሬሳም ብትሆን ግብር አጭበርብረሻል በሚል ተከሳ እንደነበር ይታወሳል። እሷ እንደምትለዉ ከሆነ ግን የምትመራዉ የዜና አገልግሎት በፊሊፒንስ መንግስት ላይ ትችት ስለሚያሰማና መንግስትን ስለሚቃወም ይህን ለማስቆም ያለመ ጥቃት እንጂ ከግብር ጋር የሚያገናኘዉ ነገር የለም ተብሏል። በተለይም የፊሊፒንሱን ፕሬዝደንት ሮድሪጎ ዱቴርቴን ክፉኛ መተቸቷ ለዚህ እንደዳረጋት ይነገራል።

የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ጉዳይም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። በተለይም ጋዜጠኛዉ በሳዉዲ ያለዉን የሰብዓዊ መብ አያያዝ መተቸቱና የንጉሳዊያን ቤተሰቦችን በተለይም ልዑል አልጋ ወራሹን ሲወርፍና ሲተች መቆየቱ ለሞት እንደዳረገው ይታወቃል።

ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአዳጊ ሀገራት ዉስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ሙያቸዉ አደገኛና ደህንነታቸዉም ስጋት ላይ የወደቀ መሆኑን ያሳያል ተብሏል።

ታይም መፅሄት በየአመቱ የሚያካሂደዉ የዓመቱ ምርጥ ሰው ምርጫ ከፈረንጆቹ 1927 ጀምሮ ሲካድ የቆየ ሲሆን በየአመቱ በበጎም ሆነ በክፉ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ለቻሉ ግለሰቦች የሚሰጥ እውቅና እንደሆነም ይነገራል።(ምንጭ: አልጀዚራ )