ትራምፕ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አጥር ለመገንባት የሚፈለገዉ በጀት እንዲመደብላቸዉ ጠየቁ

የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አጥር ለመገንባት ሚፈለገዉ በጀት እንዲመደብላቸዉ ጠይቀዋል።

ይህ የአዛዉንቱ ሰዉ የምርጫ ቅስቀሳ ጠንከር ያለ መልዕክት ነዉ።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ገና የፕሬዝደንትነት ሥልጣኑን የግላቸዉ ከማድረጋቸዉ በፊት በ2016ቱ የአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አሜሪካን ዳግም ታላቅ ስለማድረግ ህልማቸዉ ብዙ ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ሀገራቸዉን ዳግም ታላቅ ለማድረግ ሲያልሙ ደግሞ ሀገራቸዉ ለቀሪዉ አለም የምታደርገዉን ድጋፍ መቀነስ፣ ስደተኞች ወደ ሀገራቸዉ እንዳይገቡ መከልከል፣ ከጎረቤት ሜክሲኮ ጋር ያለዉን ድንበር በአጥር መዝጋትና ሌሎች እርምጃዎች እቅዴን ያሳኩልኛል ያሏቸዉ ዉጥኖች ነበሩ።

ታዲያ ሰዉየዉ ወደ ስልጣን በመጡ አጭት ጊዜ ዉስጥም ቃል የገቧቸዉን ተግባራት ተፈፃሚ ለማድረግ ጊዜ አልፈጀባቸዉም። በዚህም ከወዳጆቻቸዉ ምዕራባዊያን ሀገራትም ጭምር ሳይቀር ነቀፋን ያስከተሉባቸዉን ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ወስደዋል።

በ2016ቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገቡትን የሜክሲኮን ድንበር የማጠሩን ዉጥናቸዉንም ተግባራዊ ለማድረግ ስለመቃረባቸዉ ሰሞንኛ ወሬዎች አመላክተዋል።
ትራምፕ ከስደተኛ ጠል አቋማቸዉ ትንሽም ቢሆን ዝንፍት የማለት እቅድ ያላቸዉ አይመስሉም፣ የሜክሲኮዉን ድንበር ለመገንባት ማቀዳቸዉም ለዚሁ ነዉ።

ፕሬዝደንቱ ሜክሲኳዊያኑም ሆኑ ሌሎች ስደተኞች ለደህንነታችን ያሰጉናል፣ ወንጀልን በሀገሬ ያስፋፋሉ፣ የሀገሬን ዜጎች የስራ እድልም ይሻማሉ፣ በተጨማሪም አደንዛዥ እፆችን ወደ ሀገረ አሜሪካ በማስገባት ወጣቶቻችንን ሱሰኞች ያደርጋሉ የሚል ፅኑ እምነት አላቸዉ።

ፕሬዝደንቱ ትላንት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለአሜሪካዊያን ባስተላለፉት መልዕክታቸዉ አጥሩን መገንባት ያስፈለገዉ ሀገራችንን ከአስከፊ የሰብዓዊ ቀዉስ ለመከላከል ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ዴሞክራቶቹ ናንሲ ፕሎሲና ቸክ ሹመር የፕሬዝደንቱን አጥር የመገንባት ዉጥን መቃወም ተከትሎ ስለመሆኑም ተነግሯል።

ፕሬዝደንቱ በጉዳዩ ላይ ከኮንግረስ ሰዎች ጋር ባለመግባባታቸዉ ምክኒያት የፌደራል መስሪያ ቤቶች ለ18 ቀናት ያክል ተዘግተዉ መቆየታቸዉ የሚታወስ ነዉ። ይህም በሀገሪቱ ታሪክ ሁለተኛዉ ረዥሙ የፌደራል መስሪያ ቤቶች የተዘጉበት ጊዜ ሲሆን በዚህም በርካታ ዜጎች ያለክፍያ መቆየታቸዉ አሜሪካዊያኑን አስቆጥቷል። ዴሞክራቶቹ የኮንግረስ አባላትም ቢሆኑ የፕሬዝደንቱ አሁናዊ አካሄድ አሜሪካዊያንን የሚጎዳ ነዉ የሚል ወቀሳን አቅርበዋል።
ሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት ትራምፕ በበኩላቸዉ ያቀዱትን የሜክሲኮ ድንበር በብረት አጥር ለመገንባት 5.7 ቢሊየን ዶላር አልያም 4.5 ቢሊየን ዩሮ ገንዘብ ኮንግረሱ እንዲያፀድቅላቸዉ ይሻሉ።

የሀገሪቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ የያዙት ዴሞክራቶች ግን የፕሬዝደንቱን ሀሳብ ዉድቅ አድርገፈዉታል።

ፕሬዝደንቱ በበኩላቸዉ የዴሞክራቶቹን ሀሳብ ዉድቅ በማድረግ ለፌደራል መስሪያ ቤቶቹ መዘጋት የዴሞክራቶቹ ድርቅና ነዉ ሲሉ ይሞግታሉ። በተለይም 90 በመቶ የሚሆነዉ ወደ አሜሪካ የሚገባ የሄሮይን እፅ ከሜክሲኮ መግባቱ በርግጥም በሀገራቱ መካከል ያለዉ አጥር በአፋጣኝ መገንባት እንዳለበት የሚያሳይ ነዉ ይላሉ። ትራምፕ አክለዉም ከዚህ ቀደም ዴሞክራቶቹም ቢሆኑ የአጥር ግንባታዉን ሲደግፉ መቆየታቸዉን አንስተዋል።

የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፕሎሲና የሴኔቱ አባል የሆኑት ቸክ ሹመር  ትራምፕ የፌደራል መስሪያ ቤቶቹ ወደ ስራቸዉ እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል።

የኒዉዮርኩ ሴናተር ቸክ ሹመር በበኩላቸዉ የፕሬዝደንቱ አስተዳደር ምክኒያታዊነት ይጎድለዋል፣ ከእዉነታ ይልቅ በፍራቻ ነዉ ሀገርን መምራት እየሞከረ ያለዉ ሲሉ ወቅሰዋል። 

እንደ ዴሞክራቶቹ ሴናተሮች ሀሳብ ከሆነ ቢሊየን ዶላሮችን ወጪ አድርጎ አጥር ከመገተር ይልቅ አሁን ባለዉ አሰራር በድንበር አከባቢ ያለዉን ጥበቃ ማጠናከርና የሰዉ ሀይል ቁጥሩን መጨመር ፕሬዝደንቱ ከሚሉት የብረት አጥር የተሻለና ብዙ ወጪም የሚያስወጣና ዉጤታማ ነዉ።

በርግጥ አሜሪካ ካለባት ደህንነት ስጋት አንፃር ዴሞክራቶቹም ሆኑ ሪፐብሊካኖቹ የተሻለ የድንበር ላይ ጥበቃ እንደሚያስፈልግ ቢስማሙም የፕሬዝደንት ትራምፕ ግን እጅጉን የተጋነነ አ3ንደሆነ ይነገራል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የህገወጥ ስደተኞች ቁጥር በፈረንጆቹ 2000 1.6 ቢሊየን የነበረ ሲሆን ባለፈዉ አመት ግን ወደ 4መቶ ሺ መዉረዱ ተመላክቷል። ከዛም ባለፈ የመኖሪያ ፍቃድ ያላገኙት ስደተኞችን ቢሆኑ ወንጀሎችን የመፈፀም እድላቸዉ አናሳ መሆኑን ጥናቶች አመላተዋል።

ሰሞኑን በተካሄደ ጥናትም 51 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካዊያን ፕሬዝደንቱን አካሄድ ተቃዉመዉታል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ እቅዳቸዉን ለማሳካት ሌሎች እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉም ተንታኞች ግምታቸዉን አስቀምጠዋል፣ በተለይም ፕሬዝደንቱ የሌሎችን ድጋፍ አግኝተዉ እቅዳቸዉ ካልሰመረ በቅርቡ የመከላከያ ተቋሙ በጀት ለአጥሩ ግንባታ እንዲዉል ዉሳኔ ማስተላለፋቸዉ እንደማይቀር ይጠበቃል ። (ምንጭ: ቢቢሲ )