በሲሪላንካ በደረሰው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር 290 ደርሷል

በሲሪላንካ በደረሰው የፍንዳታ ጥቃት የሟቾች ቁጥር እስካሁን 290 መድረሱ ተገለፀ፡፡

ፍንዳታው የደረሰው ለሆሳዕና በዓል ስነ ስርአት በተሰበሰቡ አማኞች እና በኮከብ ሆቴሎች ሲሆን ከሞቱት ውጪ 500 ሰዎች መጎዳታቸው ተነግሯል፡፡

ክስተቱ በሀገሪቱ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2009 ከደረሰው የእርስ በርስ ግጭት ወዲህ የተሰማ አሳዛዛኝ ዜና ነውም ተብሏል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዌክለርማሲንግ አስቀድሞ የፀጥታ ሀይሉ ጥቃት እንደሚደርስ መረጃ ደርሶት እንደነበርና ሆኖም ተገቢው ምላሽ አለመሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ጥቃት ከደረሰ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነቶች ስድስት ጥቃቶች ተከታትለው መድረሳቸውን የሀገሪቱ መገኛኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡

በዚህም ኔጎምቦ፤ባቲካሏ ኮቺካዴ ሶስት ቤተ እምነቶች ለሆሳዕና የተሰበሰቡ አማኞችን ኢላማ ያደረገ እና በሌሎች ሻንሪላ፤ኪንግስበሪና ሲኖሞን በተባሉ ባለኮከብ ሆቴሎች ላይ ተከታታይ ትቃት መድረሱ ተነግሯል፡፡፡፡

ሌሎች ስፍራዎችን አካቶ በጥቅሉም ዘጠኝ ጥቃቶች መድረሳቸው ነው የታወቀው፡፡

ዘግይተው የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ አየር ማረፊያ አካባቢ ለፍንዳታ ማቀነባበሪያ የሚውል መሳሪያ መገኘቱን የሀገሪቱ አየር ሀይል ገልጿል፡፡

1 ነጥብ 8 ሜትር ርዝመት ያለው ተቀጣጣይ ነገር በውስጡ የያዘ PVC pipe መሳሪያ መገኘቱን ያስታወቁት የአየር ሀይሉ ቃል አቀባይ  ጀን ሳኔቫርቼን ናቸው፡፡

 

ያም ሆኖ ግን እስካሁን ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩ ነው የተገለጸው፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስራ ያዋለቸው 24 ተጠርጣሪዎችም ማንነታቸውና የትኛውን አካል እንደሚወክሉ የተባለ ነገር የለም፡፡

የቢቢሲ ዘገቢ ዛም አሜን ያካባቢውን ባለስልጣናት ጠቅሶ ከጥቃቱ ጀርባ አክራሪ ቡድኖች ሳይኖሩ እንዳልቀሩ ዘግቧል፡፡

ጥቃቱ ከመድረሱ አስቀድሞ ተገቢው ጥንቃቄና  እርምጃ አለመወሰዱ ግን አሁንም የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

የሲሪላንካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባስታወቀው መሰርት ከሟቾች መካከል 36ቱ የሌላ ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡

ይንን ተከትሎም መላው አለም ከሁሉም አቅጣጫ ሀዘኑን እየገለጸ ነው፡፡ የቫቲካኑ ጳጳስ ፈርንሲስ ድርጊቱን አረመኔያዊ ወንጅል ሲሉ ኮንነውታል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተርየስም በተመሳሳይ ድርጊቱን ያወገዙ ሲሆን ጥፋተኞችም ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት መንግስታተትም በዚህ ጸያፍ ተግባር የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ሳምንታት በፊት በመስጂድ ጥቃት 50 ንጹሃን የሞቱባት ኒውዚላንድ ጠ/ሚ ጃሲንዳ አርደን ጥቃት አድራሾችን በጋራ ለፍትህ ማቅረብ አለብን ብለዋል፡፡/ቢቢሲና አልጀዚራ/