አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለች

ኢራን ከ2015ቱ የኒዉክለር ስምምነት በከፊል እንደምትወጣ ማሳወቋን ተከትሎ አሜሪካ አዲስ ማዕቀብ በሀገሪቱ ላይ ጥላለች።

ኢራን በ2015 ከስድስት ኃያላን መንግስታት ጋር የገባችዉን የኒዉክለር ስምምነት በከፊል እንደምትሰርዘዉ መግለጿን ተከትሎ የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አዲስ ማእቀብ በኢራን ላይ መጣላቸዉን ይፋ አድርገዋል።

ይህም ቀድሞዉኑ በቋፍ ላይ የነበረዉን የሁለቱን ሀገራት ዉጥረት ወደለየለት መካረር ሊወስደዉ ይችላል የሚል ስጋት እንዲያይል አድርጓል።

ትራምፕ ትላንት ይፋ ያደረጉት ማዕቀብ በኢራን የአልሙኒየም፣ የመዳብና የብረት ዘርፎች ላይ ትኩረቱን ማድረጉ ደግሞ ምናልባትም ዘርፉ ለኢራን ምጣኔ ሀብት ከሚያስገኘዉ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ አንፃር ማዕቀቡ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚኖረዉ ተፅእኖ ከባድ እንደሚሆን ተገምቷል።

ከኋይት ሀዉስ የወጣ መረጃ እንዳመላከተዉ የኢራን የብረት ንግድ ሀገሪቱ ነዳጅ ነክ ካልሆኑት የዉጭ ግብይቷ ከምታገኘዉ ገቢ ከፍተኛዉን መጠን የሚይዝ ሲሆን ይህም 10 በመቶ የሚሆነዉን የዉጭ ንግድ ገቢ ይሸፍናል።

ከዛም ባለፈ ፕሬዝደንት ትራምፕ ኢራን አድባ የማትቀመጥ ከሆነ ተጨማሪ ማዕቀቦች ይጠብቋታል ማለታቸዉ በርግጥም የሀገራቱ መካረር ከምጣኔ ሀብታዊ ሽኩቻም በዘለለ ሀገራቱን ጦር እስከማማዘዝ ሊደርስ ይችላል ተብሏል።

በእርግጥ ለአሁኑ የኢራን ዉሳኔ አሜሪካ ባለፈዉ አመት ላይ ከስምምነቱ እራሷን ማግለሏ ዋነኛዉ ምክኒያት ስለመሆኑም ተነግሯል።

የሀገራቱን ሰሞንኛ ዉዝግብ ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት በጉዳዩ ላይ ያላቸዉን አቋም በማሳወቅ ላይ ናቸዉ።

የአሜሪካዉን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዎን በለንደን ተቀብለዉ የመከሩት የእንግሊዙ አቻቸዉ ጀርሚ ሀንት የ2015ቱ የኒዉክለር ስምምነት የምእራቡ አለም ዲፕሎማሲ ካሳካቸዉ ዉጤቶች አንዱ ነዉ ሲሉ ሀገራቸዉ የስምምነቱን መከበር እንደምትደግፍ አስታዉቀዋል።

ኢራን በከፊል ከስምምነቱ እራሷን ለማግለል ማቀዷን ተከትሎ የሀገሪቱ ቀጣይ እርምጃ ያሰጋቸዉ የአሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዎ በበኩላቸዉ ሀገራቸዉ ከእንግሊዝ የተለየ አቋም እንዳላትና ኢራንም ብትሆን በቀጣይ ምን ልታደርግ እንደምትችል በቅርበት እንደሚከታተሉ ይፋ አድርገዋል።

ሌላኛዋ የስምምነቱ ፈራሚ ሀገር ፈረንሳይ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል የኢራን ከስምምነቱ መዉጣት መዘዙ የከፋ እንደሚሆን አስታዉቃለች።

የስምምነቱን መጣስ እጅጉን የምትቃወመዋ ጀርመንም ብትሆን ሂደቱ የአለምን ሰላም ስጋት ላይ የሚጥል ነዉ ብላዋለች።

ሩስያ በበኩሏ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ በኩል ባስተላለፈችዉ መልዕክት ኢራን እዚህ ዉሳኔ ላይ ለመድረሷ የአሜሪካ ሃላፊት የጎደለዉና ግዴለሽ እርምጃ ዋነኛዉ ምክኒያት ስለመሆኑ ገልፃለች።

አሜሪካ በኢራን የቢዝነስ እንቅስቃሴና የነዳጅ ግብይት ላይ የጣለችዉ ማዕቀብ ለአሁኑ የኢራን ምላሽ መነሻ ስለመሆኑ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ አመላክተዋል።

ላቭሮቭ አክለዉም ምንም እንኳን አሜሪካ ከስምምነቱ ብታፈነግጥም ሩስያ ግን ስምምነቱን አክብራ ከኢራን ጋር በአጋርነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ቻይናም ብትሆን ጉዳዩን ሰምታ ዝምታን አልመረጠችም። በዚህም ኢራን ስምምነቱን አክብራ ለመስራት ቁርጠኛ እንደነበረችና ለስምምነቱ መጣስ ዋነኛዋ ተጠያቂ አሜሪካ ስለመሆኗ ገልፃለች።

ትራምፕ ከአመት በፊት ሀገራቸዉን ከ2015ቱ የኢራን የኒዉክለር ስምምነት ሲያስወጡ ከፍተኛ ድጋፍ ከቸሩት የአለም መሪዎች አንዱ የእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ነበሩ። ኢራን የኒዉክለር ግንባታዋን ለማስቀጠል ማቀዷን ሲሰሙም ይህን ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም የኢራንን ከስምምነቱ የመዉጣት ፍላጎት ተከትሎ አለም ስምምነቱን ስለማስቀጠል ማሰብ እንደሚጀምር ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ጉቴሬዝ ከአመት በፊት አሜሪካ ከስምምነቱ ስትወጣ ዉሳኔዉን ክፉኛ የተቃወሙ ሲሆን የአሁኑ የኢራን አካሄድም ለአለም ሰላም አስጊ በመሆኑ የስምምነቱ ፈራሚ ሀገራት ቃላቸዉን መጠበቅ እንደሚኖርባቸዉ አሳስበዋል፡፡

(ምንጭ፡- አልጀዚራ)