ዶናልድ ትራምፕ ወደ ጦርነት ከተገባ “የኢራን ፍጻሜ” እንደሚሆን ዛቱ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የግንኙነት መሻከር ተከትሎ ‹‹ኢራን ልትገጥመን ከፈለገች በይፋ ፍጻሜዋ ይሆናል›› ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እሑድ ዕለት ባስተላለፉት የትዊተር መልዕክታቸው ደግሞ ‹‹ሁለተኛ አሜሪካንን ብታስፈራሪ ወዮልሽ›› ዓይነት ዛቻ በኢራን ላይ ሰንዝረዋል፡፡
በቅርቡ አሜሪካ ተጨማሪ የጦር መርከቦችንና የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ወደ ባሕረ ሰላጤው ሀገራት አካባቢ አስጠግታለች፡፡
የትራምፕ መልዕክት ደግሞ ከዚህ በፊት ከነበረው የንቀት ንግግር ወጣ ብሎ ዛቻ ማዘሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት እንዳይፈጠር አስግቷል፡፡
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ‹‹ኢራን ኑክሊዬር እንድትታጠቅ አንሻም፤ ወደ ጦርነት መግባት አንፈልግም፤ ጦርነት ምጣኔ ሀብትን ይጎዳል፣ ሰዎችንም ይገድላል›› ብለዋል፡፡ ይህም ወደ ግጭት ማምራታቸው እንደማይቀር አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በእርግጥ በኢራንም በኩል ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከትናንት በፊት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጦርነት እንዲኖር አንሻም፤ ግን በቀጠናው የሚያውኩን ከተፈጠሩ አይቀር ይሆናል›› ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙሀመድ ጃቫድ ዛሪፍ ለሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፡፡ 
አንድ የኢራን ከፍተኛ የጦር መኮንን ለሌላ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያዬት ደግሞ ‹‹ኢራን ጦርነት አትፈልግም፤ አሜሪካኖች ግን ለግጭት እየተጋበዙ ነው፤ አያደርጉትም ብለንም አናምንም›› ብለዋል፡፡
አሜሪካና ኢራን በኑክሊዬር የጦር መሣሪያ ዙሪ ለዘመናት እንደተወዛገቡ የቀጠሉ ሀገራት ናቸው፡፡ በተለይ አሜሪካ ኢራን የኑክሊዬር የጦር መሣሪያ እንዳትታጠቅ በበርካታ ማዕቀቦች የማዳከም ሥራ ለዓመታት እየሠራች ነው፡፡ ኢራን ከ2015 (እ.አ.አ) ጀምሮ ገብታ ከነበረችበት የኑክሊዬር ስምምነት ራሷን አግልላለች፤ ምክንያቷ ደግሞ ‹‹ስምምነቱን አሜሪካ አስቀድማ ጥሳዋለች›› የሚል ነው፡፡ እንደ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጀርመን ያሉ ሀገራትም ኢራን በስምምነቱ እንድትቆይና አሜሪካም ስምምነቱን እንድታከብር እየወተወቱ ነው፡፡ ነገር ግን ውትወታው ፍሬ ያፈራ አይመስልም፡፡ የሁለቱ ሀገራት መካረርም ከቀን ቀን እየጨመረ ነው፡፡
(ምንጭ፡- ቢቢሲ)