ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለምርጫ 2020 ቅስቀሳ ጀመሩ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለ2020ው ፕሬዚደንታዊ  ምርጫ በይፋ ቅስቀሳ መጀመራቸው  ተሰምቷል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ለሁለተኛ ጊዜ አሜሪካን ለመምራት የሚያስችላቸውን ድምፅ ለማግኘት በፍሎሪዳ ኦርላንዶ ደጋፊዎቻቸውን መቀስቀስም ጀምረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የአሜሪካን የፕሬዝዳንትነት መንበር ከተቆናጠጡ በኋላ በአወዛጋቢ ባህሪያቸው እና በሚከተሉት ፖሊሲ አለምን ሲያስደምሙ ቆይተዋል፡፡

በተለይ በስደተኞች ላይ፤ በአለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ እና በመካከለኛው ምስራቅ እና ኢራን ጉዳይ የያዙት አቋም በበርካታ አሜሪካዊያን ዘንድ አሁን አሁን ድጋፍን ሲያስገኝላቸው እየተስተዋለ ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ በሚከተሉት የንግድ ፖሊሲ በአሜሪካ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጡ እና ስራ አጥነትን በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሱ ሲመሰሰከርላቸው ይደመጣል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ ዙር የስልጣን ዘመናቸውን ለማጠናቀቅ አሁን የ581 ቀን እድሜ ብቻ ይቀራቸዋል፡፡እናም ፕሬዝዳንቱ በ2020 ለሚያደርጉት የሁለተኛ ዙር የምርጫ ፉክክር ቅስቀሳቸውን ከአሁኑ ጀምረዋል፡፡

ትራምፕ ትላንት ማክሰኞ ምሽት በፍሎሪዳ ኦርላንዶ ከባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ጋር በመሆን ለደጋፊዎቻቸው በሁለት አመት ተኩል የስልጣን ዘመናቸው ያሳኳቸውን ስኬቶች  በማወውራት ዳግም እንዲመርጧቸው ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በስልጣን በቆዩባቸው ጊዚያት አሜሪካን ታላቅ ለማድረግ ብዙ መስራታቸውን አንስተዋል፡፡

አሜሪካን ከመሯት ፕሬዝዳንቶችም በ2 አመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ የተሻለ ስኬቶቸችን ማምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በተለይ ደግሞ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማስቀረት ለአሜሪካ ሀያልነት እና ለዜጎቿ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው መስራታቸውን ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ገልፀዋል፡፡

የአሜሪካ ኢኮኖሚ እድገቱን ይዞ እንደሚቀጥል እና ሪፐብሪካኑ ፕሬዝዳንትም ጠንካራ ደጋፊዎች እንዳሉት የገለፁት ትራምፕ ለቀጣይ ምርጫም ከእርሳቸው ጋር እንዲጓዙ በሺዎች ለሚቆጠሩ የፍሎርዳ ነዋሪች ገልፀዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በሚከተሉት የጠነከረ የንግድ እና የስደተኞች ፖሊሲ በብሄርተኛ አሜሪካኖች መወደድን ቢፈጥርላቸውም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞችን የማዘዋወወር ስራ እንደሚጀምሩ  ለደጋፊዎቻቸው ገልፀዋል፡፡

ትራምፕ በ2020ው ምርጫ ከተቀናቃኛቸው ዲሞክራቶች ከ20 በላይ እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከሯቸው ሲሆን ከፓርቲያቸው ሪፐብሊካን ከቢል ዌልድ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል፡፡/ቢቢሲ/