የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ሰሜን ኮሪያን አቀኑ

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ከሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር ለመገናኘት ወደ ሰሜን ኮሪያ አቅንተዋል።

ቻይና ከጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2005 ወዲህ ወደ ሰሜን ኮሪያ ይፋዊ ጉብኝት ስታደርግ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከዚህ ቀደም በቻይና ለአራት ጊዜ ያህል የተገናኙ ሲሆን፣ በምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችና በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራሞች ዙሪያ ይወያያሉ ተብሏል።

ሰሜን ኮሪያ የቻይና ዋነኛ የንግድ አጋሯ ነች።

የፕሬዝዳንት ሺ ጉብኝት የተሰማው የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ በጃፓን ከመካሄዱ ከሳምንት በፊት ነው። ፕሬዝዳንቱ በጃፓን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል።

ትራምፕና ኪም በየካቲት ወር ላይ ሀኖይ ላይ ከተገናኙና በሰሜን ኮሪያ የኒውክለር ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ውይይት ያለውጤት ከተበተነ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ውይይት ነው ተብሏል።

ላለፉት 14 ዓመታት አንድም የቻይና መሪ ወደ ሰሜን ኮሪያ አምርቶ የማያውቅ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሺም ስልጣን ላይ ከወጡበት ከ2012 ወዲህ ያደረጉት የመጀመሪያው ጉብኝት መሆኑ ተገልጿል።

በቻይናና በሰሜን ኮሪያ መካከል ካለፉት ዓመታት ወዲህ እየዋዠቀ የመጣው የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማሻሻል የተደረገ ጉብኝት ነው ሲሉ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሁለቱ መሪዎች ስላልተሳካው የሀኖይ ውይይትና ስለተቋረጠው የሰሜን ኮሪያ የኒውክለር ፕሮግራም ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጉዳዩ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎች እንደሚሉት ፕሬዝዳንት ሺ በወቅቱ ምን እንደተፈጠረና ነገሮችን እንዴት ወደ ፊት ማራመድ እንደሚቻል በመወያየት ከዚህ ውይይታቸው ያገኙትን የአሜሪካው ፕሬዝዳንትን ሲያገኙ ያቀርቡታል ይላሉ።

ይህ ጉብኝት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይሰማ እንጂ ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 70 ዓመታት ስለሆናቸው ጉብኝቱ ያልተጠበቀ ሊሆን አይችልም ያሉ ባለሙያዎችም አሉ።

በዚህ ጉብኝት የቻይና ዋነኛ ግብ የሚሆነው የሰሜን ኮሪያ መረጋጋትና የምጣኔ ኃብቱን ትብብርን ማሳደግ ነው ያሉ ባለሙያዎች ደግሞ ከዚህ ባሻገርም በሰሜን ኮሪያ የኒውክለር ፕሮግራም ንግግር ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወት ትፈልጋለች ሲሉ ይናገራሉ።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ደግሞ ይህንን ጉብኝት ዛሬም የቻይና ድጋፍ እንዳላቸው ለማሳያነት ይጠቀሙበታል ይላሉ ባለሙያዎች።

ሁለቱ ኮሚኒስት ሀገራት የረዥም ጊዜ የትብብር ታሪክ ያላቸው ወዳጅ ሀገራት ቢሆኑም ባለፉት አስርታት ግን የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራም በቻይና በበጎ አልታየም።

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)