የአሜሪካ ሴኔት ለሳዑዲ አረቢያ የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥ ወሰነ

አሜሪካ ለሳዑዲ አረቢያ በቢሊየን ዶላሮች የሚገመት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለማድረግ ተስማምታ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ሴኔቱ ስምምነቱን አግዷል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀንደኛ ተቀናቃኟ ኢራን ሳውዲን ስጋት ውስጥ ከታታለች በሚል ሰበብ የኮንግረሳቸውን አቋም ተላልፈው ከሳውዲ ጋር የስምንት ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ ነበር።

በሪፐብሊካን የሚመራው ሴኔቱ ግን ትናንት ይህን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት በሚያስቆምባቸው ሶስት የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

ውሳኔውም ለትራምፕ ትልቅ ኪሳራ ነው ተብሏል።

ዴሞክራቶች የሚቆጣጠሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የስምምነቱን ተግባራዊነት ለመግታት ተመሳሳይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

ትራምፕ በስምምነቱ መሰረት የጦር መሳሪያ ለመሸጥ አቅደው የነበረው ለሳዑዲ አረብያ ብቻ ሳይሆን ለተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ዮርዳኖስም ጭምር ነበር።

ትራምፕ ባለፈው ወር ስምምነቱን እውን ያደረጉት ብዙም ተግባራዊ ሆኖ የማያውቅ የአገሪቱን የፌደራል ህግ መሰረት በማድረግ ነበር።

ትራምፕ ቦምብን ጨምሮ ለሳውዲ በአፋጣኝ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን መሸጥ ያስፈለገው ሳዑዲን ተቀናቃኟ ኢራን አጣብቂኝ ውስጥ ስለከተተቻት ነው ቢሉም የምክር ቤቱ አባላት ግን የጦር መሳሪዎቹ በየመን ጦርነት ንፁሃን ዜጎችን ለማጥቃት ሊውሉ ይችላሉ የሚል ፍርሃት ስምምነቱን በጣም ተቃውመውታል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)