የሆንግ ኮንጓ መሪ የተቃዋሚዎችን ድርጊት አወገዙ

የሆንግ ኮንጓ መሪ ካሪ ላም የትላንቱን የተቃዋሚዎች ድርጊት አውግዘዋል።

ትላንት ተቃዋሚዎች የሆንግ ኮንግን ሕግ አውጪ ምክር ቤት ጥሰው ገብተው እንዳልነበረ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የመብት ተሟጋቾች በአደባባይ እያደረጉ የነበረው ተቃውሞ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ከተቃውሞው ወጥተው ወደ ሕግ አውጪ ምክር ቤት በማምራት ለሰዓታት እቃ ሰባብረዋል።

መሪዋ ተግባሩን "የሚያሳዝንና ብዙዎች ያስደነገጠ" ብለውታል።

ትላንት ሆንግ ኮንግ ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ በቻይን ሥር የወደቀችበትን 22ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሰላማዊ ተቃውሞ እየተደረገ ነበር።

እለቱ በየዓመቱ የሚታሰበው ስለዴሞክራሲ መስፈን በሚያወሳ ሰልፍ ሲሆን፤ ዘንድሮ ግን በሆንግ ኮነግ የነበረውን የሳምንታት ጠንካራ ተቃውሞ ተከትሎ መጥቷል።

ሆንግ ኮንግ ውስጥ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ለቻይና ተላልፈው ይሰጡ የሚል ረቂቅ ሕግ መቅረቡን ተከትሎ ሆንግ ኮንግ በተቃውሞ እየተናጠች ትገኛለች።

ትላንት ቀትር ላይ ይደርግ የነበረው ተቃውሞ አካል የነበሩ ጥቂት ሰልፈኞች ተነጥለው ወደ ምክር ቤት አቅንተው ጥቃት ሰንዝረዋል።

የምክር ቤቱን የመስታወት ወለል ሰባብረው ወደ ውስጥ በመዝለቅ፤ የሆንግ ኮንግን ሰንደቅ አላማ አንስተው፤ ግድግዳው ላይ በደማቅ ቀለም መልዕክት አስፍረዋል። የተለያዩ ቁሳቁሶችንም ሰባብረዋል።

ይህን ተከትሎ መሪዋ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ "ተግባሩን ሁላችንም ማውገዝ አለብን። ማህበረሰቡ ወደ ቀደመ ሰላሙ በቅርብ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።