አሜሪካ የባህረ ሰላጤውንና የየመን የውሃ አካላትን ለመቆጣጠር ወታደራዊ ጥምረት ልትመሰርት ነው

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ የጦር ኃላፊ በኢራንና የመን አከባቢ የሚገኙ የውሃ አካላትን ለመቆጣጠር አሜሪካ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ጥምረት መመስረት እንደምትፈልግ አስታወቁ።

የባሕር ኃይሉ ጀኔራል ጆሴፍ ደንፎርድ ወሳኝ የንግድ መስመር በሆነው ቀጠና ''በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ማረጋገጥ ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ከአንድ ወር በፊት በሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ በተፈጸመው ጥቃት በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎችን አሜሪካ ተጠያቂ ታደርጋለች።

ጀኔራል ጆሴፍ ደንፎርድ የአሜሪካን ዕቅድ ለማስፈጸም ''የፖለቲካ ዝግጁነት'' እና አቅም ካላቸው ሃገራት ጋር አሜሪካ ንግግር እያደረገች ነው ብለዋል።

አሜሪካ ትዕዛዝና ቁጥጥር የሚያደርጉ መርከቦችን ታሰማራለች፤ የሌሎች ሃገራት ሚና የሚሆነው እነኚህን መርከቦች ማጀብ ነው ብለዋል።

በፋርስና በኦማን ባህረ ሰላጤዎች መካከል ያለው ሰርጥ እንዲሁም የመን፣ ጅቡቲና ኤርትራን የሚያዋስነው ባብ ኤል-ማንዳብ ሰርጥ ወሳኝ የንግድ መርከቦች መተላለፊያና ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም ቀይ ባሕርን የሚያገናኙ ናቸው።

በየቀኑ በባብ-ኤል ማንዳብ በኩል ለተቀረው ዓለም የሚጓጓዘው የነዳጅ መጠን እስከ 4 ሚሊዮን በርሜል ይገመታል።

የአሜሪካ እቅድ ግዝፈት የሚወሰነው በተሳታፊ ሃገራት መጠን እንደሚሆን ጀኔራሉ አልሸሸጉም።

''የተሳታፊዎቹ ሃገራት ብዛት አነስተኛ የሚሆን ከሆነ፣ አነስተኛ ተልዕኮ ይኖረናል። የተሳታፊዎች ቁጥር በጨመረ መጠን የምንዳስሰው ስፍራ ከፍ ይላል'' ብለዋል።

ከአንድ ወር በፊት ሁለት ነዳጅ የጫኑ መርከቦች ላይ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ወዲህ አሜሪካ በቀጠናው ያላት ፍላጎት እጅጉን ጨምሯል።

መርከቦቹ ላይ ለደረሰው ጥቃት አሜሪካ ኢራንን ተጠያቂ ብታደርግም ኢራን ግን ከደሙ ንጹህ ነኝ ብላለች። ይህ ጥቃቱ ካጋጠመ ከአንድ ቀን በኋላ ደግሞ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን በኢራን ተመትቶ በባህረ ሰላጤው ላይ ወድቋል።

ኢራን ድሮኑን መትታ ከጣለች በኋላ የአየር ክልሏን ጥሶ መግባቱን በመጥቀስ፤ ይህ እርምጃዋ ''ለአሜሪካ ግልጽ የሆነ መልዕክት ነው'' ብላለች።

አሜሪካ በበኩሏ ድሮኑ ተመትቶ ሲወድቅ ዓለም አቀፍ የአየር ክልል ላይ ነበር የሚገኘው ስትል ድርጊቱን ኮንናለች። በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ''ኢራን ትልቅ ስህተት ፈጸመች'' በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አሜሪካ ለአጸፋዊ እርምጃ የአየር ጥቃት ለመሰንዘር አቅዳ የነበረ ቢሆንም ዘግይቶ እቅዱ ተሰርዟል።

ኢራን የነዳጅ ምርቷን ወደ ውጪ መላክ የማትችል ከሆነ የሆርሙዝ መተላለፊያን እንደምትዘጋ ዝታለች፤ በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን ወደ ኒውክሌር ስምምነቱ የማትመለስ ከሆነ የነዳጅ ምርቷን ለገበያ እንዳታቀርብ ማዕቀብ እጥላለሁ እያሉ ያስፈራራሉ።

''ኢራን ከማንም ጋር ወደ ጦርነት መግባት አትፈልግም ይሁን እንጂ ኢራንን ለመከላከል ዝግጁ ነን'' በማለት የኢራን የጦር ጀኔራል የአሜሪካንን ድሮን መትተው ከጣሉ በኋላ ተናግረው ነበር።

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዩኬ ጋርም ፍጥጫ ውስጥ ናት፣ የብሪታኒያ መንግሥት ሰኔ ላይ ሁለት የነዳጅ ታንከሮች ላይ በደረሰው ጥቃት የኢራን እጅ እንዳለባት" ከሞላ ጎደል እርግጠኛ" ነን ማለቷን ተከትሎ ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)