እንግሊዝ የነዳጅ መርከቧ በኢራን በመታገቱ ስጋት ገብቷታል ተባለ

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የእንግሊዝ ባንዲራን ታውለበልብ የነበረች ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ኢራን የወሰደችው "ተቀባይነት የሌለው እርምጃ" በእጅጉ "ስጋት ውስጥ እንደከተተው" ገለጸ።

ትናንት በኢራን የታገተችው መርከብ ስቴና ኢምፔሮ የምትሰኝ ሲሆን፣ በኢራን ሪቮሉሽነሪ ጋርድ በቁጥጥር ስር መዋሏን የዘገበው ፋርስ የዜና ተቋም ነው።

የመርከቡ ባለቤቶች መርከቡ ስትራይት ኦፍ ሆርሙዝ በተባለው የውሃ ክልል ላይ በኢራን መንግሥት ከታገተች በኋላ ከመርከቡ ሰራተኞች ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።

ኢራን በበኩሏ መርከቧ "ዓለም ዓቀፉን የባህር ኃይል ደንብ ተላልፋለች" ስትል ከስሳለች።

የመርከቧ ባለቤቶች መርከቧ በዓለም አቀፉ የውሃ ክልል ላይ ስትደርስ "የዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ደንቦችን በሙሉ አክብራ ስትንቀሳቀስ ነበር" ብለዋል።

የድርጅቱ ኃላፊ የሆኑት ኢስተር ሀንት እንዳሉት፤ ምንም እንኳ የዓለም አቀፉ ሕግጋትን አክብራ እየተንቀሳቀሰች ቢሆንም የኢራን ባህር ሀይል በአራት ጀልባዎችና ከላይ በሂሊኮፕተር በመታገዝ ከበባ በመፈፀም ከነበረችበት የዓለም አቀፉ የውሃ ክልል ወደ ኢራን የውሃ ክልል ተወስዳለች ብለዋል።

በመርከቢቷ ላይ 23 ሠራተኞች የነበሩ ሲሆን፣ የሕንድ፣ የሩሲያ፣ የላቲቪያና የፍሊፒንስ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በሰራተኞቹ ላይ ግን የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተዘገበ ነገር የለም።።

የኢራን ባህር ኃይል ሌላ የእንግሊዝ መንግሥት ንብረት የሆነች ነገር ግን የላይቤሪያን ባንዲራ የምታውለበልብ መርከብ በቁጥጥር ስር አውለው የነበረ ቢሆንም ወዲያው ግን መልቀቃቸው ተሰምቷል።

የእንግሊዝ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ በማዋቀር ትናንት ሁለት ጊዜ የተሰበሰበ ሲሆን፤ የኮሚቴው ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በኢራን ተቀባይነት የሌለው ተግባር በእጅጉ ስጋት ገብቶናል" ብለዋል።

አክለውም ኢራን በዓለም አቀፉ የውሃ ክልል ላይ ለሚኖረው ቀዘፋ ተግዳሮት ነው ያስቀመጠችው ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

"ለጊዜው የዩናይትድ ኪንግደም መርከቦች ከዚህ የውሃ ክልል እንዲርቁ ነው ምክራችንን የምንለግሰው" በማለት የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ ይህ ጉዳይ በፍጥነት መፍትሄ የማያገኝ ከሆነ ጠንከር ያሉ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

"ወታደራዊ እርምጃን እንደመፍትሄ እያየን አይደለም፤ በመፍትሄነት ያቀረብነው ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን ነው፤ ነገር ግን በፍጥነት መፍትሄ መገኘት አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የኢራን ተግባር የተሰማው በአሜሪካ በዩናይትድ ኪንግደምና በኢራን መካከል ያለው ፍጥጫ እየተካረረ ባለበት ወቅት ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)