የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለድንበር አጥር ማስገንቢያ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ፈቀደ

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ ለማስገንባት ላቀዱት የግንብ አጥር 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ፈቀደ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከሜክሲኮ በምትዋሰነው ድንበር የስደተኞችን ፍልሰት ለመቆጣጠር በሚል መከላከያ ግንብ የመገንባት እቅድ አላቸው።

ለዚህም 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም÷ይህ ከኮንግረሱ ተቃውሞ ማስተናገዱን ተከትሎ ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የትራምፕ አስተዳደር ያስፈልገኛል ካለው ገንዘብ ውስጥ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላሩን ይጠቀም ዘንድ ይሁንታን ሰጥቷል።

ፈቃዱን ተከትሎም ትራምፕ በካሊፎርኒያ፣ አሪዞና እና ኒው ሜክሲኮ ግዛቶች ለሚገነባው መከላከያ ግንብ ገንዘቡን መጠቀም ይችላሉ ነው የተባለው።

ይሁንና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፈቃድ ግን ከዴሞክራቶች እና ከበርካታ ግዛቶች ተቃውሞ እንደገጠመው የዘገበው ሬውተርስ ነው፡፡