አሜሪካ በሩስያ ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች

አሜሪካ በሩስያ ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች።

ዋሺንግተን ማዕቀቡን የጣለችዉ ሩስያ በ2018 ሰርጌ እስክሪፓል የተባለን የእንግሊዝ ሰላይ በኬሚካል ንጥረ ነገር መርዛለች በሚል ምክንያት ነዉ ተብሏል።

የቀድሞዉ የሩስያ ወታደራዊ የስለላ ሰዉ ሰርጌ እስክሪፓል ሀገሩ ሩስያን ክዶ ለእንግሊዝ የስለላ ስራን ሲያከናዉን በነበረበት በፈረንጆቹ 2018 በእንግሊዟ ሳሊስበሪ ከተማ ከሴት ልጁ ሁሊያ ስክሪፓል ጋር በአንድ የገበያ ማዕከል አካባቢ ተመርዞ አደጋ ላይ መውደቁ ይታወሳል።

በወቅቱ ሴት ልጁን በሞት ያጣው ሰርጌ እስክሪፓል ሩስያ ሰራሽ በሆነና ነርቭን በሚያጠቃዉ ኖቪቾክ የተሰኘ ንጥረ ነገር በመመረዙ ነበር፤ በድርጊቱ የሩሲያ የረዘመ የሩስያ እጅ እንዳለበት አሜሪካና እንግሊዝ የጸና እምነት አሳድረው ቆይተዋል።

ሩስያ አሁንም ድረስ ክሱን መሰረተ ቢስ ስትል በተደጋጋሚ ብታጣጥለዉም፤ በወቅቱ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በበሩስያ ላይ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ፤ አሁን ላይ ደግሞ ከሰርጌ እስክሪፓል መመረዝ ጋር በተያያዘ በሞስኮ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ስለመጣሏ ተሰምቷል።

የአሜሪካ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባወጣዉ መግለጫ፤ ከዚህ በኋላ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለሩስያ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ አሜሪካ በፅኑ እንደምትቃወም አመላክቷል ተብሏል።

አሜሪካ ወደ ሩስያ የምትልካቸዉን የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና ሌሎች ለኬሚካል ቅመማ፣ ለጦር መሳሪያ ምርት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን መጠን በከፍተኛ መጠን እንደምትቀንስ የአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ሞርጋን ኦርታገስ አስታዉቀዋል።

ማዕቀቡ ሞስኮ ከዋሺንግተን ጋር በነበራት የሁለትዮሽ የንግድ ትስስር የምታገኘዉን ቢሊዮን ዶላሮች የሚያሳጣት ይሆናልም ተብሏል።

ማዕቀቡ ከቀጣዩ የፈረንጆቹ ነሃሴ 19 ጀምሮ ለ15 ቀናት ከሚዘልቀዉ የኮንግረንስ አባላት ምክክር በኋላ ወደ ትግበራ ይገባል የተባለ ሲሆን፤ የ12 ወራት ቆይታ እንደሚኖረዉም ይጠበቃል ተብሏል።

ከአሁኑ የአሜሪካ ማዕቀብ አስቀድሞም የአዉሮፓ ህብረትም ባለፈዉ የፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ በዘጠኝ የሩስያና የሶርያ ባለስልጣናት ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።ዘገባው የኤ.ኤፍ.ፒ ነው።