ሰሜን ኮሪያ “የሳይበር ጥቃትን በመጠቀም ሁለት ቢሊዮን ዶላር መስረቋ” ተገለጸ

ሰሜን ኮሪያ የጦር መሣሪያ መርሃ ግብሯን ለመደጎም “2 ቢሊዮን ዶላር በሳይበር ጥቃት መስረቋን” ሾልኮ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ይፋ አደርጓል።

ፒዮንግያንግ ገንዘቡን ለመሰብሰብ ባንኮችን እና በኢንተርኔት ሲስተም የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦችን ዒላማ ማድረጓን ነው ምሥጢራዊ ሪፖርቱ የጠቆመው።

የተመድ የዘርፉ ጠበብቶች የ'ሳይበር ማይኒንግ' ድርጊቶችን ማለትም እጅግ የረቀቁ ኮምፒዩተሮችን በመጠቀም የሚደረጉ የውጭ ገንዘብ የመመንተፍ ድርጊቶች ላይ ምርመራ እያካሄዱ ይገኛሉ።

ሪፖርቱ ለተባበሩት መንግስታት ደርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ምርመራ ለሚያደርገው ኮሚቴ የተዘጋጀ ነው።

ከሳይበር ጥቃቱ ባሻገርም ከዚህ በፊት ሰሜን ኮሪያ ተጥሎባት የነበረውን ከመርከብ መርከብ የእቃዎች ሽግግር መፈፀሟን የሚገልፁ መረጃዎችም በሪፖርቱ ተካተዋል።

ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር የጀመረችው ድፕሎማሲ ጥረት አልሳካ ሲላት የተለያዩ ርቀት ያላቸው ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ተከትሎ ዳግም ቀጠናው ወደ ውጥረት ተመልሷል።

(ምንጭ፦ ቢቢሲ)