በሆንግ ኮንግ አዉሮፕላን ጣቢያ ለሶስት ቀናት የሚዘልቅ አዲስ ተቃዉሞ መቀስቀሱ ተሰማ

በቻይናዋ እራስ ገዝ አስተዳደር ሆንግ ኮንግ አዉሮፕላን ጣቢያ ለሶስት ቀናት የሚዘልቅ አዲስ ተቃዉሞ መቀሳቀሱ ተሰማ፡፡

በቻይናዋ እራስ ገዝ አስተዳደር ሆንግ ኮንግ ወንጀል ፈፅመዉ ጥፋተኛ የሚባሉ ዜጎች ለፈጸሙት ወንጀል ከቻይና መንግስት ፍርድ እንዲሰጣቸዉ የሚያስችል ህግ መዉጣቱን ተከትሎ የግዛቲቱ ነዋሪዎች ህጉን በመቃወማቸዉ ሆንግ ኮንግ ለወራት በህዝባዊ አመፅ ስትናወጥ ቆይታለች።

ለሶስት ወራት የዘለቀዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ማብቂያዉ መች እንደሆነ ዛሬም በዉል የታቀወ ነገር የለም።  

አልጀዚራ ባስነበበዉ መረጃ በግዛቲቱ አዉሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ለሶስት ቀናት የሚዘልቅ አዲስ ተቃዉሞ ተቀስቅሷል። ተቃዋሚዎቹ በአዉሮፕላን ጣቢያዉ ድምፃቸዉን ያሰሙት በአዉሮፕላን ጣቢያዉ የሚመላለሱ አለም አቀፍ ተጓዦች የችግሩን መጠን እንዲረዱና አለም አቀፉ ማህበረሰብም በጉዳዩ ላይ የበኩሉን ተፅእኖ እንዲያሳድር በማሰብ ነዉ ተብሏል።

የተቃዉሞዉ ዳግም መቀስቀስን ተከትሎ የሆንግ ኮንጓ ዋና አስተዳዳሪ ካሪ ላም መንግስታቸዉ ተቃዋሚዎችን የሚለማመጥበት ትዕግስት እንደሌለዉና አስፈላጊዉን እርምጃ ለመዉሰድ መሰናዳቱን አስታዉቀዋል።

በቼክ ላፕ ኮክ አዉሮፕላን ጣቢያ የተሰባሰቡት ተቃዋሚዎቹ ጥቁር ቲሸርቶችን የለበሱና ቁጥራቸዉም በመቶዎች የሚቆጠር ስለመሆኑ ተነግሯል። ተቃዋሚዎቹ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ተቃዉሟቸዉን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማድረስ መሰል ተቃዉሞ ያካሄዱ ሲሆን፣ የአሁኑም ለሁለተኛ ጊዜ ስለመሆኑ ተነግሯል።

ተቃዉሞዉን ተከትሎም የአዉሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዉ ኃላፊዎች በአከባቢዉ ያለዉ የፀጥታ ኃይል እንዲጠናከርና የአዉሮፕላን መሳፈሪያ ቅፅ ያልያዙ ሰዎች ወደ ቅጥር ግቢዉ እንዳይገቡ እግድ ጥለዋል።

የአሁኑ ተቃዉሞ ከመንግስት አካላት እዉቅና የሌለዉ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በአዉሮፕለን ጣቢያዉ የተደረጉ የተቃዉሞ ሰልፎች ግን በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቃቸዉ ነዉ የተሰማዉ። በመሆኑም ምንም እንኳን ተቃዉሞዉ ቢኖርም የአዉሮፕላን ጣቢያዉ መደበኛ ስራዉን እያከናወነ ስለመሆኑ ተገልጿል።

የአልጀዚራዉ ሰዉ ሮብ ማክብራይድ ከስፍራዉ እንደዘገበዉ የአዉሮፕላን ጣቢያዉ ተቃዉሞ ይልቅ የግዛቲቱን ባለስልጣናት ስጋት ዉስጥ የከተታቸዉ በቀጣይ ቀናት ሀመላዉ ሆንግ ኮንግ ይካሄዳል ተብሎ የተሰጋዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ነዉ።

በሆንግ ኮንግ የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ ካስከተለዉ የፀጥታ መደፍረስ ባለፈ የግዛቲቱን ምጣኔ ሀብትም ክፉኛ እየጎዳዉ ስለመሆኑ መረጃዎች አመላክተዋል። በግዛቲቱ ኃላፊዎች ይፋ የተደረገ መረጃ እንዳመላከተዉ ባለፈዉ ወር መጨረሻ ላይ የነበረዉ የቱሪስት ፍሰት ከባለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ26 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።   

ይህ ደግሞ በግዛቲቱ ነዋሪወፖች ላይ የሚያስከትለዉ ምጣኔ ሀብታዊ ቀዉስ የከፋ እንደሚሆን ነዉ የሚጠበቀው። በሆንግ ኮንግ ለ250ሺ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረዉ የቱሪዝም ዘርፉ 4.5 በመቶ የሚሆነዉን የግዛቲቱን ምጣኔ ሀብት ዘርፍም ይሸፍናል።

የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ካሪ ላምም ለወራት የዘለቀዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ያስከተለዉን ምጣኔ ሀብታዊ ቀዉስ ሱናሚ ሲሉ ከአስከፊዉ የአዉሎ ንፋስ ወጀብ ጋር አመሳስለዉታል።

የሆንግ ኮንጉ ተቃዉሞ ግዛቲቱ በፈረንጆቹ 1997 ከእንግሊዝ ለቻይና ተላልፋ ከተሰጠች ወዲህ ከፍተኛዉ ስለመሆኑ አልጀዚራ በዘገባዉ አስታዉሷል።