ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ለመሸጥ ያፀደቀችውን የጦር መሳሪያ የምትተገብር ከሆነ አፀፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ገለጸች

ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ለመሸጥ ያጸደቀቸውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ የምትወስድ መሆኑን አስታውቃለች።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለታይዋን የሚከናወን የ8 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል ያፀደቁ ሲሆን፤ በውሉ መሰረትም ዋሽንግተን 8 ቢሊንየን ዋጋ ያላቸው ኤፍ 16 የተሰኙ ተዋጊ ጄቶችን ለታይዋን የምትሸጥ ይሆናል።

ይህን ተከትሎም ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ለመሸጥ ያፀደቀችውን የጦር መሳሪያ ውል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትሰርዝ በድጋሚ አስጠንቅቃለች።

የቻይና  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹኒንግ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ፈጣን ምላሽ ፤አሜሪካ ልታከናውነው ያፀደቀቸው የጦር መሳሪያ ሽያጭ የቻይናንና  አንድነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ነው ።

ስለሆነም አሜሪካ በቀጠናው ከምታከናውናቸው ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ልትቆጠብ ይገባል ብለዋል፡፡

አሜሪካ ማሳሰቢያውን ወደ ጎን በመተው የመሳሪያ ሽያጩን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ  ቻይና ጠንከር ያለ አጸፋዊ እርምጃ የምትወስድ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህ ምክንያት ለሚፈጠረው ችግር  አሜሪካ ሃላፊነቱን ትወስዳለች ያሉት ሁዋ ቹኒንግ፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ዋሽንግተ ጉዳዩን በድጋሜ እንድታጤነው አሳስበዋል።

ቻይና አሜሪካ ለታይዋን ጦር መሳሪያ ለመሸጥ ስታቅድ ጀምሮ ድርጊቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ስታስጠነቅቅ መቆየቷን አስታውሶ የዘገበው ፕረስ ቲቪ ነው።