ጠ/ሚ ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከዌስት ባንክ ይዞታ ከፊሉን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ማቀዳቸውን የአረብ አገራት ተቹ

የአረብ አገራት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከዌስት ባንክ ይዞታ ከፊሉን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ማቀዳቸውን ተችተዋል።

የሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደውን የእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ፤ እቅዱ እንደሚተገበር ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። የጆርዳን፣ የቱርክ እና የሳዑዲ አመራሮች እቅዱን በጥብቅ ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በእቅዳቸው የጠቀሷቸው ጆርዳን ቫሊ እና ዴድ ሲ የዌስት ባንክ አንድ ሦስተኛ ይዞታ ሲሆኑ፣ የአረብ ሊግ እቅዱን "አደገኛ" እና "ኃይል የተሞላው" ሲል ኮንኖታል። ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጻረር እቅድ ነውም ብለዋል።

የፍልስጤሙ ዲፕሎማት ሳዒብ ኤራካት "ይህ እርምጃ ወንጀል ነው፤ የሰላም ጭላንጭልን ያዳፍናል" ብለዋል።

እስራኤል ከጎርጎሮሳውያኑ 1967 ጀምሮ ዌስት ባንክን ይዞታዋ ብታደርግም በቁጥጥር ሥር ግን አልዋለም ነበር። ፍልስጤም ነፃ አገርነቷን ስታውጅ ይህ ቦታ ግዛቷ እንደሚሆን ትገልጻለች።

እሰራኤል ደህንነቷን ለመጠበቅ ስትል በጆርዳን ያላትን ይዞታ እንደማትለቅ ጠቅላይ ሚንስትሩ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት ከምረጡኝ ቅስቀሳቸው ጋር በተያያዘ ነው። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ካደረጉ በዌስት ባንክ ያሉ የአይሁዳውያን ሰፈራዎችን እንደሚጠቀልሉም ገልጸዋል።

ኔታንያሁ የሚመሩት ፓርቲ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ከፍተኛ ፉክክር እያደረገ ይገኛል። የቢቢሲ የመካከለኛው ምስራቅ ተንታኝ ቶም ቤትማን እንደሚለው፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ እቅድ የቀኝ ዘመሞችን ድጋፍ ለማግኘት ያለመ ነው።

ከኔታንያሁ ፓርቲ በተቃራኒው ያለው የ 'ብሉ' እና 'ዋይት' ፓርቲዎች ጥምር መሪ ያሪ ላፒድ "እቅዱ ያለመው ድምፅ ለማግኘት እንጂ ግዛት ለማግኘት አይደለም" ብለዋል።

የጆርዳን ጠቅላይ ሚንስትር አይማን ሳፋዲ እቅዱ "አካባቢውን ዳግመኛ ወደ ቀውስ የሚወስድ ነው" ብለዋል።

የቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜቩልት ካቩስጎሉ እቅዱን "ዘረኛ" ሲሉ ኮንነውታል።

የሳዑዲ አመራሮችም እቅዱን ተችተው የ'ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ኢስላሚክ ኮኦፕሬሽን' 57 አባል አገራትን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡