3 ሚሊየን የሶሪያ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ነው

3 ሚሊየን የሶሪያ ስደተኞች ደህንነታቸው በተሻለ ሁኔታ እንዲጠበቅ ያስችላል ወደ ተባለ ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ሊመለሱ እንደሚችሉ የቱርኩ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ራሲፕ ጣይፕ ኤርዶሃን እንዳሉት ከማንኛውም አይነት አደጋ ነጻ የሆነው አካባቢ ከአሜሪካመንግስት  ጋር  በመተባባር የተዘጋጀ መዘጋጀቱንና ደህንነቱን አስተማማኝ ለማድረግ ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ የሚደገፉት የኩርድ ተዋጊዎች ቀደም ብሎ በቱርክ ድንበር በኩል ካለው የሶሪያ ሰርጥ ለቅቀው መሄዳቸው የሚታወስ ነው። ቱርክ ደግሞ የኩርድ ተዋጊዎችን በአሸባሪነት ፈርጃቸዋለች።

የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ዕቅድ ይፋ የሆነው አንካራ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሳን ሮሃኒ ጋር ውይይት ካደረገች በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ምንም እንኳን የኩርድ ተዋጊዎች ስለፕሬዝዳንቱ አስተያየት ያሉት ነገር ባይኖርም አምርረው እንደሚቃወሙት ግልጽ ነው ብሏል የቢቢሲው የሶሪያ ዘጋቢ አላን ጆንስተን፡፡

በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ቱርክ ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በምታደርገው ጥረት ዓለማ አቀፍ ድጋፍ የማታገኝ ከሆነ ስደተኞቹ ወደ አውሮፓ አልፈው እንዲሄዱ ድንበሯን ክፍት እንደምታደርግ ገልጻ ነበር።

ቱርክ በድንበሯ በኩል ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት እንዳይሞክሩ ጠበቅ ያለ ጥበቃ ማድረግ እንዳለባት እ.አ.አ በ2016 ከአውሮፓ ህብረት ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት ስምምነት ተደርሷል፡፡

ቱርክ ይህንን በማድረጓና ከሶሪያ የሚመጡ ስደተኞችን በማስተናገዷ ከአውሮፓ ህብረት 6.6 ቢሊየን ዶላር እንደምታገኝ ቃል ተገብቶላት ነበር። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ኤርዶአን ቃል ከተገባው ገንዘብ ግማሽ የሚሆነው ብቻ ነው የደረሰን ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ 6 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚሆነውን ገንዘብ ለቱርክ አስረክቢያለሁ ብሏል።

ቱርክ በ2011 የተጀመረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ሸሽተው የወጡ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን በተለያዩ ማቆያዎች ይዛለች።

በቱርክ ድንበር በኩል የምትገኘው ኢድሊብ ግዛት በአማጺያን እና ኢስላማዊ ጂሃዲስቶች ቁጥጥር ስር በመሆኗ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ከቅያቸው ወደ ሰሜናዊ ሶሪያ ተሰድደዋል።