ኢራን የአውሮፓ አገራትን ውንጀላ አጣጣለች

ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደም በጥምረት፤ በሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ ከደረሰው ጥቃት ጀርባ ያለችው ኢራን ናት ቢሉም፤ ኢራን ውንጀላቸውን አጣጥላዋለች።

የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የሦስቱን አገራት ክስ "የአሜሪካን ከንቱ ክስ ያስተጋባ" ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።

የአውሮፓ አገራት መሪዎች እንዳሉት፤ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ከኢራን ውጪ ማንም ላይ ጣት መቀሰር አይቻልም። ኢራን የምትደግፈው የየመኑ የሁቲ አማጽያን ቡድን ጥቃቱን የሰነዘርኩት እኔ ነኝ ሲል ኃላፊነቱን ቢወስድም፤ አሁንም ተጠያቂ የተደረገችው ኢራን ናት።

ስምንት ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሰባት ሚሳኤሎች የሳዑዲን የነዳጅ ማቀነባበሪያ ከመቱ በኋላ፤ ሳዑዲ እንዲሁም አሜሪካ ኢራንን ወንጅለዋል። ኢራን በበኩሏ በጥቃቱ እጄ የለበትም ማለቷ ይታወሳል።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኗ መራሔተ መንግስት አንግላ መርኬል በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ኢራን ለጥቃቱ ተጠያቂ ናት ብለዋል። እየተካሄደ ያለውን ምርመራ እንደሚደግፉም አሳውቀዋል።

"ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ለድርድር ዝግጁ መሆን የሚጠበቅባት ጊዜ ላይ ነን" ሲሉም መሪዎቹ ተናግረዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2015 ላይ የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት (ጆይንት ኮምፕሪሄንሲቭ ፕላን ፎር አክሽን) በማክበር እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስምምነቱ አገራቸውን አውጥተው ኢራን ላይ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ ሁለቱ አገራት ተፋጠዋል።

ፕሬዘዳንት ትራምፕ "የቀድሞው ስምምነት ብዙ ችግሮች አሉት። አዲስ እና ከቀደመው የተሻለ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ ነኝ" ካሉ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ሀሳቡን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ቦሪስ ከኢራኑ ፕሬዘዳንት ጋር እንደሚገናኙም ተነግሯል።

የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሞሀመድ ዣቪድ ዛሪፍ፤ አዲስ የኒውክሌር ስምምነት እንደማይረቀቅ ገልጸዋል። አሜሪካ ከስምምነቱ በመውጣቷ ሦስቱ የአውሮፓ አገራትም ከስምምነቱ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ አለመሆኑንም አክለዋል።

"አሁን ያለው ስምምነት ሳይከበር አዲስ ስምምነት አይረቀቅም" ብለዋል።

አሜሪካ እና አጋር አገራት፤ የሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ ለደረሰው ጥቃት ወታደራዊ ምላሽ ለመስጠት ከቃጡ፤ ኢራን አጸፋውን እንደምትመልስም ተናግራለች። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)