ፕሬዝዳንት ትራምፕን ከስልጣናቸው ለማስወገድ በአሜሪካ ምክር ቤት ድምጽ እንዲሰጥባቸው ሊደረግ ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስልጣናቸው እንዲወገዱ የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት /ኮንግረስ/ ድምጽ እንዲሰጥባቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ከወዲሁ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱ ድምጹን የሚሰጠው በአውሮፓዊያኑ 2016 በተደረገው የፕሬዝዳንት ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ የወቅቱን ተቀናቃኛቸውን ለማሸነፍ በሚል በዮክሬን ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና አድርገዋል የሚል ክስ ስለቀረበባቸው መሆኑን ተነግሯል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ በሃላ የፖለቲካ ተፎካካሪያቸውን ጆን ባይደንና ልጃቸውን ዩክሬን በሙስና እንድትከሳቸው፣ አለበለዚያ ግን አሜሪካ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታቆም ጫና አድርገዋል በሚል ነው ዴሞክራቶች ክሱን ያቀረቡት፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጉዳዮ ትክክል እንዳልሆነና የፈጠራ ወሬ እንደሆነ አድርገው ክሱን አጣጥለውታል ተብሏል፡፡

በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫውን ድምጽ የያዙት ዲሞክራቶች በመሆናቸው ክሱን ገፍተው ከሄዱበት ፕሬዝዳንቱን ከስልጣናቸው ለማንሳት የሚሰጠው ድምጽ በአመዛኙ ይሁንታ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይሁን እንጂ በአገሪቱ ሴኔት አብላጫ ወንበር የያዙት ፕሬዝዳንቱን የሚደግፉት የሪፐብሊካን ፓርቲ በመሆናቸው የዴሞክራቶች ውሳኔ በሴኔቱ ውድቅ የመደረግ እድሉ ሰፊ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ (ምንጭ፡-ቢቢሲ)