የሳኡዲ አረቢያው ንጉሥ ጠባቂ በጥይት ተገደለ

የሳኡዲው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ የግል ጠባቂ የነበረው ግለሰብ ከጓደኞቹ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ተተኩሶበት መገደሉን ባለስልጣናት አስታወቁ።

ጀነራል አብደል አዚዝ አል ፋጋም ቅዳሜ ምሽት ላይ ነበር ጓደኛውን ለመጠየቅ በሄደበት ከሞሃመድ ቢን ሚሻል ሰል አሊ ጋር ግጭት ተፈጥሮ ለሞት የበቃው።

የፖሊስ መግለጫ እንደሚያመለክተው ሁለቱ ግለሰቦች ከተጋጩ በኋላ አሊ የተባለው ተጠርጣሪ ጅዳ ሁለቱ ከነበሩበት ቦታ ወጥቶ በመሄድ ሽጉጥ ይዞ በመመለስ ተኩስ ከፍቷል።
ተኳሹም ለፖሊስ እጁን እንዲሰጥ ቢጠየቅም እምቢ በማለት ተተኩሶበት መሞቱ ተገልጿል። ጀነራል ፋጋም በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምከንያት ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ አልፋለች።

በተጨማሪም ሌሎች ሰባት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል። ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ሁለቱ የሟች ጀነራል ፋጋም ጓደኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ግን የደህንነት አባላት ናቸው ተብሏል።

ጀነራል ፋጋም በብዙ የሳኡዲ ዜጎች ዘንድ የሚታወቅ ሲሆን ከንጉሥ ሳልማን ጋርም የቅርብ ግንኙነት ነበረው። ለብዙ ዓመታትም የንጉሡ ግል ጠባቂ ሆኖ አገልግሏል።

ብዙዎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች 'ጀግና' ነበር እያሉ አሞካሽተውታል።