ሰሜን ኮሪያና አሜሪካ እንደገና ድርድር ሊጀምሩ ነው

የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት በሁለቱ አገራት የተቋረጠውን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ንግግር መልሶ ለማስጀመር ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ድርድር መልሶ ለማስጀመር ሲዊዲን ገቡ።

በፕሬዝዳንት ትራምፕና በሰሜን ኮሪያው መሪ መካከል በመጨረሻ የተደረገው ውይይት ያለስምምነት ነበር የተጠናቀቀው።

ከዚያ በኋላ ሁለቱም አገራት ድርድሩን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም ብዙም የጎላ እርምጃ ሳያሳይ ቆይቷል።

የአሁኑ የንግግር ፈቃደኝነት የመጣው ሰሜን ኮሪያ ቀደም ካሉት ሙከራዎቹ ከፍ ባለ ሁኔታ አዲስ ሚሳኤል ለሙከራ ከተኮሰች ከቀናት በኋላ ነው።

ይህ ሚሳኤል ባሕር ላይ ከሚገኝ ማስወንጨፊያ ላይ የተተኮሰ ሲሆን፣ ከባሕር ሰርጓጅ መርከብ ሊተኮስም ይችላል፤ ይህም ማለት ሰሜን ኮሪያ ከግዛቷ ውጪ ሚሳኤሎችን የማስወንጨፍ ብቃት እንዳላት ያመለክታል።

ሰሜን ኮሪያ ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን እንዳትጠቀም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እገዳ የተጣለባት ሲሆን፤ እያካሄደችው ባለው የኒዩክሌር ግንባታ ፕሮግራም ምክንያት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባታል።

ከሲዊዲኗ ዋና ከተማ ስቶክሆልም ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ሊዲንጎ በተባለችው ደሴት ላይ በሚካሄደ የሁለቱ አገራት ድርድር ላይ የአሜሪካ የሰሜን ኮሪያ ልዩ ተወካይ ስቴፈን ቢገን እንዲሁም የሰሜን ኮሪያው ኪም ጊል ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)