ቱርክ የአሜሪካን የተኩስ አቁም ጥሪ ውድቅ አደረገች

ቱርክ የአሜሪካን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪ ውድቅ አድርጋለች፡፡ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶሃን ጦሩ ማጥቃቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የጣይብ ኤርዶሃን አስተያየት የተሰማው ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ማይክ ፔንስና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፒዮ ወደ ቱርክ ለመብረር በተዘጋጁበት ወቅት ነው።

ሁለቱ የአሜሪካ ሹማምንት በቱርክና በኩርዶች መካከል ሰላም እንዲወርድ ይጥራሉ ተብሏል።

የተኩስ አቁም በፍፁም አናውጅም ያሉት ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን፣ አክለውም " ጫና እያሳደሩብን ያሉት እርምጃችንን እንድናቆም ነው። ማዕቀብም ጥለዋል። ዓላማችን ግልፅ ነው። ስለማዕቀቡ አንጨነቅም" ብለዋል።

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት " ቱርክ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ካልተስማማችና ካልተገበረች" እንዲሁም በድንበሩ አካባቢ ስደተኞችን ለማስፈር ለመደራደር ፈቃደኛ ካልሆነች ማዕቀቡ ይበልጥ እንደሚጠብቅ አስጠንቅቀዋል።

ቱርክ ኩርዶችን ከድንበር አካባቢ ማራቅ የዚህ ጥቃቷ ግብ እንደሆነ በፕሬዝዳንቷ በኩል ደጋግማ ተናግራለች።

በኩርዶች የሚመራው የሶሪያ ዲሞክራቲክ ግንባር በቱርክ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ነው።

አንካራ ከዚህ ቀደም በድንበሩ አቅራቢያ 30 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን "ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠና" መመስረት እንደምትፈልግ አስታውቃለች። በዚህ ስፍራም ቱርክ የሚገኙ 2 ሚሊየን ሶሪያውያን ስደተኞችን የማስፈር ዕቅድ አላት።

በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ በሩሲያ የሚደገፉ የሶሪያ ወታደሮች ከኩርዶች ጋር በመደራደር በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ላይ በመግፋት የቱርክ ወታደሮችንና አፍቃሪ ቱርክ አማፂያንን ርምጃ ለመግታት ሞክረዋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ጦር ከቀጠናው መውጣቱ በተገለፀበት ቅፅበት ቱርክ ጦሯን በሶሪያ የድንበር ከተሞች በማዝመት መጠነ ሰፊ ጥቃት መክፈቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡።

ይህንን የአሜሪካ መንግሥትን እርምጃ የሚተቹ አካላት የአሜሪካ ድርጊት ለቱርክ ጥቃት ይኹንታን የሰጠ ነው ይላሉ።

አሜሪካ ግን ይህንን በማስተባበል ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።

እስካሁን ድረስ በርካታ ተዋጊዎች ሲሞቱ ከ160 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።